ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች በክህሎት የበቁ ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት ጥራት ያለውን ስልጠና መስጠታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የጋሞ ዞን ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መምሪያ አሳሰበ።
በደቡብ ምዕራብ ሲኖዶስ የአርባ ምንጭ መካነ ኢየሱስ ቴክኒክ ኮሌጅ ‘ከአድራ ጀርመን ፕሮጀክት’ ጋር በመተባበር በሶላር ፓኔል ተከላ እና ጥገና ዙሪያ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ3ኛ ጊዜ አስመርቋል።
የደቡብ ምዕራብ ሲኖዶስ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ኦርካዶ ኦልቴ እንዳሉት፥ ከመንፈሣዊ አገልግሎት በተጓዳኝ በልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ከ30 በላይ የልማት ዘርፎች የአከባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረጉን አስረድተዋል።
የጀርመን የልማት ድርጅት ከደቡብ ምዕራብ ሲኖዶስ የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ጋር በመተባበር በሶላር ኢነርጂ ተከላና ጥገና ዙሪያ ለሶስኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ወጣቶች ማስመረቁ ሥራ አጥነትን ከመቀነስ ባለፈ ለታዳሽ ሀይል ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ የጎላ ነው።።
ስልጠናው የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ እና ታዳሽ ሀይል ዕሳቤ ተግባራዊ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑም ተብራርቷል።
ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ተግባር ተኮር በመሆኑ ሰልጣኞች ክህሎታቸውን ተጠቅመው ሥራ ፈጥረው እንዲሠሩ ያግዛቸዋል ያሉት የአርባ ምንጭ መካነ ኢየሱስ ኮሌጅ ዲን አቶ አደን አብዱሩሐማን ናቸው።
አያይዘውም ኮሌጁ በተለያዩ የስልጠና መስኮች ተማሪዎችን እያሰለጠነ ሲሆን በአጫጭር ኮርሶች ደግሞ በታዳሽ ሀይል ዘርፍ በ”ግሪን ኢነርጂ ቲቪቲ ከአድራ ጀርመን ፕሮጀክት” ጋር በመተባበር ለሶስተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 43 ሰልጣኞችን ማስመረቁንም አብራርተዋል።
የጋሞ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ሀላፊ አቶ ወንድሙ ኡቶ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት ቴክኖሎጂን በማስፋፋት እና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ባለመ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ ኮሌጆች ልምድ የሚቀሰሙባቸው እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግባቸው ለመሆን ጥራት ያለውን ስልጠና መስጠታቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
ካነጋገርናቸው ሰልጣኞች መካከል ወ/ሮ ታብሌት ታምራት እና ጴጥሮስ ሳሙኤል እንዳሉን በስልጠና ቆይታቸው የተግባር ተኮር እና ንድፈ ሐሳቦችን መቅሰማቸው በቀጣይ ብቁ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ሰልጣኞች ከእንግዶች እጅ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸውዋል።
ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
“ትንንሽ የሚመስሉ ስራዎች ለትልልቅ ዕድሎች በር ይከፍታሉ” – ወይዘሮ ህልውና ጌታቸው
የህግ ታራሚዎችን በስነ ምግባር ለማነፅ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ገለፀ
ሰላምን ማጽናት የጸጥታ ተቋማት ዋነኛ ተልዕኳቸው ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)