1 ሺህ 47 ማልያዎችን የሰበሰበው የሊቨርፑሉ ደጋፊ
ፍሎሪያን ተርለር የተባለ ስዊዘርላንዳዊ የሊቨርፑል ደጋፊ የመርሲሳይዱን ክለብ 1 ሺህ 47 ማልያዎችን በመሰብሰብ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ተመዝግቧል።
የሊቨርፑል የልብ ደጋፊ የሆነው ግለሰብ የአንድ እግር ኳስ ክለብ ማልያዎችን ብቻ በመሰብሰቡ ነው ስሙ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ የሰፈረው።
ፍሎሪያን ተርለር ነዋሪነቱ በስዊዘርላንድ ማግሊንገን በምትባል መንደር ሲሆን ከ4 ቀናት በፊት 60ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ሲያከብር ለ5 አስርተ ዓመታት ሲሰበስብ የቆየውን የእንግሊዙን ክለብ ማልያ በአንድ የእግር ኳስ ማዘውተሪያ ስፍራ ላይ በማንጠፍ ዓለምን ጉድ አሰኝቷል።
እንደ ሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ፤ ተርለር ከዚህ ቀደም እግር ኳስን በያንግ ቦይስ ተጫውቶ ቢያሳልፍም ከልጅነቱ ጀምሮ ግን የሊቨርፑል ደጋፊ ነው ተብሏል።
በዚህም እንደ አውሮፓውያኑ ከ1950ቹ አንስቶ እስካሁን የመርሲሳይዱን ክለብ ምልክት የሆኑ ትጥቆችን ሰብስቦ ማኖሩ ተገልጿል።
ከሰበሰባቸው ትጥቆች መካከል ሊቨርፑል እንደ አውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ ላይ የመጀመሪያውን ዩሮፒያን ካፕ ሲያነሳ እንዲሁም በእንግሊዝ እግር ኳስ ላይ በነገሰበት በ1980ዎቹ የውድድር ዓመታት የተጠቀማቸው ማልያዎች ይገኙበታል።
በተጨማሪም ሊቨርፑል በ2019 ከ14 ዓመታት በኋላ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ሲያነሳ እና በ2020 ከ30 ዓመታት በኋላ የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ሞሐመድ ሳላህን ጨምሮ ሌሎች ከዋክብት ተጫዋቾች የለበሷቸው ዘመናዊ ማልያዎች ይገኙበታል ተብሏል።
ፍሎሪያን ተርለር የሰበሰባቸው ማልያዎች ሲሰሉ በየቀኑ የተለያዩ ማልያዎችን ለሶስት ዓመታት ሊለብስ ይችላል እንደማለት ነው።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ሀዋሳ ከተማ ጌታነህ ከበደን አስፈረመ
አርሰናል ማክስ ዶውማንን በሻምፒዮንስ ሊጉ ስብስብ አካተተ
አትሌቲኮ ሚኒዬሮ ሆርጌ ሳምፖሊን በድጋሚ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ