ሊቨርፑል ከአርሰናል ከሰዓታት በኋላ ወሳኝ ግጥሚያ ያካሂዳሉ
በ3ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር መርሐግብር ሊቨርፑል ከአርሰናል ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ ወሳኝ ግጥሚያ ያከናውናሉ።
ባለፈው የውድድር ዓመት የሊጉ የዋንጫ አሸናፊ ለመሆን ዋነኛ ተፎካካሪ የነበሩት ሁለቱ ክለቦች በአዲሱ የውድድር ዓመትም ይህንኑ ለማስቀጠል በጥረት ላይ ይገኛሉ።
ሁለቱ ተጋጣሚዎች የመጀመሪያዎቹን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፈው ነው ዛሬ የሚገናኙት።
የአሰልጣኝ አርኔ ስሎቱ ቡድን በመጀመሪያ ሳምንት መርሐግብር ቦርንማውዝን 4ለ2 እና በ2ኛ ሳምንት ኒውካስልን 3ለ2 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
የአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታው ቡድን አርሰናል በበኩሉ በመጀመሪያ ሳምንት ማንቸስተር ዩናይትድን 1ለ0 እንዲሁም በ2ኛ ሳምንት ሊድስ ሁናይትድን 5ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በአዲሱ የውድድር ጎል ያላስተናገደ ብቸኛው የፕሪሚዬር ሊግ ክለብ ሆኖ ይገኛል።
የመርሲሳይዱ ክለብ በአንፊልድ በመስከረም ወር በኖቲንሃም ፎረስት ከተረታ ወዲህ ያለፉትን 18 ተከታታይ ጨዋታዎችን ያልተሸነፈ ሲሆን የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ደግሞ በፕሪሚዬር ሊጉ ከሜዳው ውጪ ከህዳር ወር አንስቶ በ15 ተከታታይ ጨዋታዎች ሳይሸነፍ ከሜዳ ወጥቷል።
በዛሬው ጨዋታ የትኛው ክለብ ጥንካሬውን ያስቀጥላል የሚለው ትኩረትን ይስባል።
መድፈኞቹ ሊቨርፑልን በአንፊልድ ሮድ ማሸነፍ ከቻሉ 13 ዓመታት ተቆጥረዋል።
አርሰናል ወደ አንፊልድ ተጉዞ ሊቨርፑልን ለመጨረሻ ጊዜ ማሸነፍ የቻለው በ2012 ሲሆን የወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ በጊዜው ተጫዋች ነበሩ።
ከዚህ በኋላ ባሉት 13 ዓመታት የሰሜን ለንደኑ ክለብ የመርሲሳይዱን ክለብ በሜዳው ነጥብ ከመጋራት ውጭ ማሸነፍ አልቻለም፡፡
የሁለቱ ክለቦች የመጨረሻዎቹ 5 የእርስ በእርስ ግጥሚያዎች በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቁት።
ሊቨርፑል እና አርሰናል በታሪካቸው 245ኛ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን በዛሬው ዕለት የሚያከናውኑ ይሆናል።
እስካሁን በተካሄዱ 244 ፍልሚያዎች የወቅቱ የፕሪሚዬር ሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል 95 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አርሰናል 83 ጊዜ አሸንፏል። 66 ጊዜ ደግሞ ሁለቱ ክለቦች በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።
በፕሪሚዬር ሊጉ በተከናወኑ 66ቱ የሁለቱ ክለቦች ግንኙነት 198 ጎሎች ተመዝግበዋል።
በዚህም ከሰሜን ለንደን ደርቢ በመቀጠል በርካታ ጎል የተመዘገበበት የእርስ በእርስ ግጥሚያ ሆኖ ይገኛል።
በሊቨርፑል እና አርሰናል የእርስ በእርስ ግንኙነት ብዙ ጎሎችን በማስቆጠር የቀድሞ የሊቨርፑሉ አጥቂ ሮቤርቶ ፈርሚኖ ቀዳሚው ተጫዋች ሆኖ ይገኛል።
ብራዚላዊው ኢንተርናሽናል 11 ጎሎችን ሲያስቆጥር ሞሐመድ ሳላ በ10 ጎሎች ተከታዩን ደረጃ ይዟል።
የዛሬውን የሊቨርፑልን እና አርሰናልን ወሳኝ ፍልሚያ በዋና ዳኝነት የማንቸስተር ከተማው ተወላጅ ክሪስ ካቫኔጅ ሲመሩት ሚሼል ሳሊስበሪ ደግሞ የቫር ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ማንቸስተር ሲቲ በአዲሱ የውድድር ዓመት 2ኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናገደ
ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል
ጄሚ ቫርዲ ወደ ጣሊያን ሴሪኣ ሊያቀና ነው