ሮድሪ እና ዳኒ ካርቭሃል ከ12 ወራት በኋላ ወደ ስፔን ብሔራዊ ቡድን ተመለሱ

ሮድሪ እና ዳኒ ካርቭሃል ከ12 ወራት በኋላ ወደ ስፔን ብሔራዊ ቡድን ተመለሱ

ለእግርኳስ ተጫዋቾች እጅግ ፈታኝ ከሆነው የኤሲኤል ጉዳት አገግመው በቅርቡ ወደ ሜዳ የተመለሱት ሮድሪ እና ዳኒ ካርቭሃል ከ12 ወራት ቆይታ በኋላ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሷቸዋል።

አሰልጣኝ ሉይዝ ዴ ላ ፉኤንቴ ስፔን በቀጣይ ላለባት ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪ ጨዋታ ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበዋል።

የወቅቱ የባሎንዲኦር አሸናፊ ሮድሪ ባለፈው የውድድር ዓመት በፕሪሚዬር ሊጉ ከአርሰናል ጋር ሲጫወት ካጋጠመው እና ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ካራቀው ጉዳት በኋላ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ተመልሷል።

የሪያል ማድሪዱ የመስመር ተከላካይ ዳኒ ካርቭሃልም አጋጥሞት ከነበረው ተመሳሳይ ጉዳት ማገገሙን ተከትሎ በላ ሮጃዎቹ ስብስብ መካተቱ ይፋ ሆኗል።

አዲሱ የባርሴሎናው ግብ ጠባቂ ኋን ጋርሲያ እንዲሁም የሪያል ማድሪድ ተከላካዮች አልቫሮ ካሬራስ እና ራውል አሴንሲዮ ግን ጥሪ አልደረሳቸውም።

በአንፃሩ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከሪያል ቤቲስ ወደ ኮሞ የተዛወረው የ19 ዓመቱ የፊት መስመር ተጫዋች ጄሱስ ሮድሪጌዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ካሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶታል።

ከሜክሲኮው የዓለም ዋንጫ አንስቶ ያለማቋረጥ በዓለማችን ትልቁ የእግርኳስ ድግስ የተሳተፈችው ስፔን በቀጣይ ወደ 2026 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአውሮፓ አህጉር ማጣሪያ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም በቱርክ ከቡልጋሪያ እንዲሁም ጳጉሜን 2/2017 ዓ.ም ላይ ከጂዮርጅያ ጋር መርሐግብሯን የምታከናውን ይሆናል።

ዘጋቢ፦ሙሉቀን ባሳ