አርሰናል የፒኤሮ ሂንካፔን ዝውውር ከማጠናቀቁ አስቀድሞ ሁለት ተከላካዮቹ ክለቡን ሊለቁ ነው

አርሰናል የፒኤሮ ሂንካፔን ዝውውር ከማጠናቀቁ አስቀድሞ ሁለት ተከላካዮቹ ክለቡን ሊለቁ ነው

የፒኤሮ ሂንካፔን ዝውውር ለማጠናቀቅ የተቃረበው አርሰናል ሁለቱ ተከላካዮች ክለቡን ለመልቀቅ መቃረባቸው ተገልጿል።

የሰሜን ለንደኑን ክለብ ለመልቀቅ በእጅጉ ተቃርቦ የሚገኘው ተከላካይ ጃኮብ ከቪዮር ነው።

የ25 ዓመቱ የኋላ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ጃኮብ ኪቪዮር ወደ ፓርቹጋሉ ክለብ ፖርቶ ለመዛወር ከስምምነት ላይ ደርሷል።

ፖርቶ ለተከላካዩ ዝውውር ወደ 27 ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ የዝውውር ሂሳብ ለመድፈኞቹ ለመክፈል መስማማቱ ተነግሯል።

በ2023 ከጣሊያኑ ክለብ ስፔዚያ አርሰናልን የተቀላቀለው ፖላንዳዊው ተጫዋች ለሚኬል አርቴታው ቡድን 68 ጨዋታዎችን አከናውኖ 3 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ግብ የሆኑ የመጨረሻ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

አርሰናልን ለመልቀቅ የተቃረበው ሁለተኛው ተከላካይ ኦሌክሳንደር ዚንቼንኮ ነው።

ዩክሬይናዊውን ሁለገብ ተጫዋች ለማስፈረም የፈረንሳዩ ክለብ ማርሴ ድርድር ማድረግ መጀመሩ ተሰምቷል።

የ28 ዓመቱ ተጫዋች በሰሜን ለንደኑ ክለብ ያለው ኮንትራት ለመጠናቀቅ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ የቀረው ሲሆን ኦሎምፒክ ማርሴ ዚንቼንኮን በቋሚነት ለማስፈረም ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ዘ አትሌቲክ አስነብቧል።

በዚህ ክረምት እስካሁን ሰባት ተጫዋቾችን በቋሚነት ማስፈረም የቻለው አርሰናል በአንፃሩ የመስመር ተከላካዮቹ ኬሪያን ቲዬርኒ፣ ታኪሄሩ ቶሚያሱ እና ኑኖ ታቫሬስ ቡድኑን መልቀቃቸው ይታወሳል።

አርሰናል በቀጣይ ኢኳዶሪያዊውን ተከላካይ ፒኤሮ ሂንካፒዬን ያስፈርማል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ