ዣቪ ሲሞንስ አዲስ ፈላጊ ክለብ አገኘ

ዣቪ ሲሞንስ አዲስ ፈላጊ ክለብ አገኘ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርቢ ሌፕዚግ የጨዋታ አቀጣጣይ ዣቪ ሲሞንስ ሊዘጋ በተቃረበው የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ተጨማሪ ፈላጊ ክለብ ማግኘቱ ተገልጿል።

በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ በጥብቅ የሚፈለገው ኔዘርላንዳዊውን ተጫዋች ለማስፈረም ሌላኛው የለንደኑ ክለብ ቶትንሃም አዲሱ ፈላጊ ክለብ ሆኖ ብቅ ብሏል።

የፊት መስመራቸውን ለማጠናከር ሞርጋን ሮጀርስን ከኖቲንግሃም ፎረስት እንዲሁም ኤቤሪቼ ኤዜን ከክርስቲያል ፓላስ ለማስፈረም ጥረት አድርገው ያልተሳካላቸው አሰልጣኝ ቶማስ የዝውውር መስኮቱ ከመጠናቀቁ አስቀድመው ዣቪ ሲሞንስን ለማስፈረም ጥረት ማድረግ መጀመራቸው ተነግሯል።

ሌፕዚግም የ22 ዓመቱ ተጫዋች በወደፊት የእግርኳስ ህይወቱ መፍትሔ ለማበጀት እንዲረዳው ወደ ለንደን አቅንቶ ከክለቦቹ ጋር እንዲደራደር ፈቃድ እንደሰጠው ዘ አትሌቲክ አስነብቧል።

ከውጤታማው የላማሲያ አካዳሚ የተገኘው ዣቪ ሲሞንስ ከ2 ዓመት በፊት ከፒኤስጂ ነበር በቋሚ ዝውውር የጀርመኑን ክለብ የተቀላቀለው።

ከተጫዋቹ ዝውውር ወደ 70 ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ሒሳብ የሚፈልገው ሌፕዚግ የዝውውር ሂደቱ መሻሻል ካላሳየ በቀጣይ ቀናት ሲሞንስን ወደ ጀርመን ለመመለስ ዝግጁ መሆኑ ተነግሯል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ