ሁሉ አቀፍ ድጋፍ የሚሹ አካላትን መርዳት የጥቂት አካላት ተግባር ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሥራ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

ሁሉ አቀፍ ድጋፍ የሚሹ አካላትን መርዳት የጥቂት አካላት ተግባር ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሥራ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

ይህ የተገለፀው እንደክልል በአንድ ጀምበር ከ4 ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታ አካል የሆነውን በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳን ጨምሮ የቢሮ አመራሮችና ሠራተኞች ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ እንደገለፁት፤ እንደሀገር “በጎነት ለአብሮነትና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ባለፉት ሰባትና በላይ ዓመታት የተለያዩ በጎ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በዚህም በርካታ ሁሉ አቀፍ ድጋፍ የሚሹ አካላትን መድረስ መቻሉን ሀላፊዋ ገልፀው፤ ዘንድሮ እንደ ክልል በአንድ ቀን ጀምበር ከ4 ሺህ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች ገንብቶ ለማስረከብ ሲታቀድ የክልሉ ትምህርት ቢሮ በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳና ዲመካ ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በሚፈጅ ገንዘብ በሁለቱም ቦታ እያንዳንዳቸው አርባ ቅጠል ያለው ቆርቆሮ ቤት ለመገንባት አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን አስረድተዋል።

ሁላችንም በመተጋገዝ አንድነታችንን ማጠናከርና ከጎናችን ያሉ ድጋፍ የሚሹ አካላትን መርዳት አለብን ሲሉ ወ/ሮ ፀሐይ አሳስበው፤ ፓርቲው ዜጋ ተኮር አላማውን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።

የቤት ግንባታ ሥራው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለዜጎች እንዲተላለፍ እንደሚደረግ በሥራው ላይ የሚገኙና ሥራውን የሚያስተባብሩ የቢሮው ምክትል ሀላፊዎች ተናግረዋል።

በጎነት ለራስ የሚደረግ የህሊና እርካታና ከፈጣሪ ዘንድም በረከት የሚገኝበት ነው ሲሉም ገልፀዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሀላፊ አቶ ታደለ ጋያ እንደገለፁት፤ እንደዞን ከዘጠኝ መቶ በላይ ቤቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል።

በአሁን ወቅት ጥቂት እየተገነቡ ያሉ ቤቶች በአጭር ጊዜ አልቀው ለግለሰቦች እንደሚተላለፉ አቶ ታደለ አስረድተዋል።

በወረዳ ደረጃ ከ60 በላይ ቤቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ የገለፁት የበናፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ጋርሾ ናቸው።

ወ/ሮ ፒታ ካውጳ በክልሉ ትምህርት ቢሮ ቤት የሚገነባላቸው አቅመ ደካማ እናት ሲሆን ከዚህ በፊት የአየር ፀሐይ በተፈራረቀ ልክ ተቸግረው ኑሮአቸውን እንደሚመሩ አስታውሰው፤ የክልሉ ትምህርት ቢሮ በሚገነባላቸው ቤት ከችግራቸው እንደሚላቀቁ ተናግረዋል።

ስለሚደረግላቸው በጎ ሥራም አመስግነዋል።

አቅመ ደካማ እናት ከዚህ በፊት በቀበሌ አስተዳደር ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደነበርም ተገልጿል።

እንደሀገር የሚከናወኑ ዜጋ ተኮር የልማት ሥራዎች የህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ውጤት እያስገኘ እንደሆነም ተገልጿል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን