በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ኒውካስል ከሊቨርፑል ዛሬ ምሽት ይጫወታሉ

በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ኒውካስል ከሊቨርፑል ዛሬ ምሽት ይጫወታሉ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የመጨረሻ መርሐግብር በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ኒውካስል ዩናይትድ ከሊቨርፑል ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ሊቨርፑል ቦርንማውዝን 4ለ2 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ሲጀምር ኒውካስል በበኩሉ ከሜዳው ውጪ ከአስቶንቪላ ጋር 0ለ0 መለያየቱ ይታወሳል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሊቨርፑል ሻምፒዮን ሲሆን ጥንካሬውን ካሳየባቸው የሜዳ ክፍሎች መካከል አንዱ የማጥቃት መስመሩ ነው።

የመርሲሳይዱ ክለብ ክብረወሰን በሆነ መልኩ በ31 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቹ ላይ ሁለት እና ከዚያ በላይ ጎሎችን አስቆጥሮ ከሜዳ ወጥቷል።

የአሠልጣኝ አርኔ ስሎቱ ቡድን በያዝነው ዓመትም በዚህ የሜዳ ክፍል ላይ ይበልጥኑ ጥንካሬውን ለማስቀጠል ቆርጦ የተነሳ ይመስላል።

ክለቡ በመጀመሪያ ሳምንት መርሐግብር በሜዳው የአንዶኒ ኢራኦላውን ቡድን 4 ለ 2 ሲያሸነፍ ጎል ያስቆጠረውን ሁጎ ኢኪቲኬን እና የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የተካነውን ፍሎሪያን ቪርትዝን በአዲስ መልክ ወደ ስብስቡ መቀላቀሉ ይታወቃል።

የአሰልጣኝ ኤዲ ሀው ቡድን ኒውካስል ዩናይትድ በአንፃሩ ራሱን ለማጠናከር በዝውውር መስኮቱ ሁሉ አማረሽ የሚሏትን ይመስል ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር ስሙ ቢነሳም እስካሁን ግን በእጁ ያስገባው አራት ተጫዋቾችን ብቻ ነው። አንቶኒ ኢላንጋ፣ ማሊክ ቲያው፣ አሮን ራምስዴል እና ጃኮብ ራምሴ ናቸው አዲሶቹ ፈራሚዎቹ።

ከእነዚህ ተጫዋቾች መካከል ለማስፈረም ዋነኛ ኢላማቸው ሆኖ ወደ ክለቡ የመጣው አንቶኒ ኢላንጋ ብቻ መሆኑ ልብ ይሏል። ሌሎቹ ለማስፈረም ይፈልጓቸው የነበሩት ተጫዋቾች ወደ ሌሎች ክለቦች ማቅናታቸውን ተከትሎ 2ኛ እና 3ኛ ተመራጭ ሆነው ነው ወደ ሴንት ጀምስ ፓርክ ያቀኑት።

ሁጎ ኢኪቲኬን በሊቨርፑል የተነጠቁት ማግፓይሶቹ ኮከባቸውን አሌክሳንደር አይሳክንም ከብብታቸው ሊነጠቁ ተቃርበዋል።

የሁለቱ ክለቦች የምሽቱ ጨዋታ በስውዲናዊው ኢንተርናሽናል ዝውውር ምክንያት ውጥረት ውስጥ በገቡ ክለቦች መካከል የሚካሄድ ጨዋታ መሆኑን ተከትሎ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።

የ25 ዓመቱ አጥቂ በዝውውር ውዝግብ ምክንያት በጨዋታው ለነጭ እና ጥቁር ለባሾች ተሰልፎ የማይጫወት ይሆናል።

ኒውካስል ዩናይትድ አሌክሳንደር አይሳክ ባልተሰለፋባቸው ያለፉት አራት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ጎል ያላስቆጠረ በመሆኑ የእሱ አለመኖር የፊት መስመሩን ጥንካሬ ያሳሳዋል ተብሎ ይታሰባል።

ሊቨርፑል በፕሪሚዬርሊጉ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2015 ጀምሮ ላለፉት 10 ዓመታት በኒውካስል አልተረታም።

በኒውካስል በኩል በአይሳክ በተጨማሪ የቀድሞ የአርሰናል ተጫዋች ጆይ ዊሎክም በጉዳት ምክንያት የማይሰለፍ መሆኑን ተከትሎ የመስመር አጥቂው አንቶኒ በሀሰተኛ የዘጠኝ ቁጥር ሚና ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

በሊቨርፑል በኩል አዲሱ ፈራሚ ጄሬሚ ፍሪምፖን እና ጆእ ጎሜዝ ምክንያት የማይሰለፉ ሲሆን ሪያን ግራቨንበርች ግን ቅጣቱን አጠናቆ ዛሬ ምሽት ክለቡን ማገልገል ይጀመራል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ