“የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴት ከማጎልበት ባሻገር አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሰው ተኮር መርሃ ግብር ነው” – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

“የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴት ከማጎልበት ባሻገር አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሰው ተኮር መርሃ ግብር ነው” – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የአንጋፋው የጥበብ ሰው አርቲስት ፊሻሌ ሚልካኖ ጨምር የሁለት የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ በማስጀመር ክልላዊ የአንድ ጀንበር ስራ በይፋ አስጀምረዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በመከናወን ላይ የሚገኘው የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጥበብ ባለውለታ ለሆነው አርቲስት ፊሻሌን ጨምሮ ለሁለት አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ በማስጀመር በወላይታ ሶዶ ከተማ መርሃ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የአንድ ጀንበር ቤት ግንባታውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፤ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴቶች ተቋማዊ የሚያደርግና ከመንግስት ይወጣ የነበረ ከፍተኛ ሀብት በማዳን ጭምር በርካቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ የሚገኝ ፍፁም ሰው ተኮር መርሃ ግብር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አስጀማሪነት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአይነትም ሆነ በመጠን እየሰፋ መምጣቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መርሃ ግብሩ ሁሉን አሳታፊ በመሆኑም ዜጎች ለአወንታዊ ለውጥ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰብዓዊነትን የሚያስቀድምና የህሊና እርካታን የሚያስገኝ ከመሆኑም ባሻገር የዜጎችን ሕይወት ያሻሽላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በጎነት ለአብሮነት፤ ለሀገር ከፍታና ለራስ በመሆኑም በመርሃ ግብሩ ሁሉም ሊሳተፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

አክለው ያሉን የተፍጥሮ ፀጋዎች ላይ በጎነትንና ቅንነትን በማከል እርስ በርስ ከተባበርን፤ ከተጋገዝንና ከተደመርን ጊዜያዊ ችግሮቻችንን በመሻገር ባጭር ጊዜ በጥረታችን ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል።

ባለፉ ጊዜያት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የማይታለፉ የሚመስሉ ፈታኝ ወቅቶችን ከመሻገር ባለፈ የማይቻሉ የሚመስሉ በርካታ አስደናቂ ስኬቶች ማስመዝገብ የተቻለው በመተባበርና መደጋገፍ ውስጥ ባለ ኅብረትና አንድነት መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶች፤ ሴቶችና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ አቅመ ደካሞችንና አረጋዊያንን ተጠቃሚ ያደረጉ፤ የህዝብ ለህዝብ ትስስርንና አብሮነትን የሚያጎለብቱ እንዲሁም ለዘላቂ ሰላምና ልማት የጎላ ሚና ያላቸው በርካታ የበጎ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣው የበጎ ፈቃድ ተግባር ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሁም በሁሉም መስክ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በመደረግ ላይ ላለው ጥረት ትልቅ አቅም የሚፈጥር በመሆኑም በቋሚነት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በሚከናወነው የአንድ ጀንበር የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታም፤ 4 ሺህ 600 ቤቶችን በአንድ ጀንበር በመገንባት ሌላ አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ መታቀዱን ጠቅሰው፤ በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች ለታቀደው ግብ ስኬት ህብረተሰቡ በነቂስ በመሳተፍ የዚህ አኩሪ ታሪክ አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ያለንን ጉልበት፤ ዕውቀት እና ሀብት አቀናጅተን በራስ አቅም ችግሮቻችንን ለመፍታት ከተባበርን እና በኅብረት ለጋራ ልማት ከተጋን ዘላቂ ልማትንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ይበልጥ ባጠረ ጊዜ እናረጋግጣለን ሲሉ በአጽንኦት በመግለጽ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት በ2016/17 ዓ/ም የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስድስቱም የክልሉ ማዕከላት ሰባት የአረጋዊያን እና አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታን አከናውኖ በማጠናቀቅ ከነሙሉ የቤት እቃ ለባለቤቶቹ ማስረከብ መቻሉ ተገልጿል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በዘንድሮም መርሃ ግብር ወላይታ ሶዶን ጨምሮ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ባለሀብቶችንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር አስራ አንድ የአረጋዊያንና ጧሪ ያጡ አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታን የሚያከናውን መሆኑም ታውቋል፡፡