ለተማሪዎች ምዝገባ ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት አሰታወቀ

ለተማሪዎች ምዝገባ ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት አሰታወቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በልዩ ወረዳው በ2018 የትምህርት ዘመን ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ ሀሰን እንደገለፁት፥ በተጠናቀቀው በ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባርን በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

የትምህርት ስራ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረትና ተሳትፎ እንደሚጠይቅ የተናገሩት ኃላፊው፥ በ2018 የትምህርት ዘመን ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ በማስቀጠልና ውስንነቶችን በመቅረፍ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መረባረብ ይገባል ብለዋል።

በትምህርት ዘመኑ 12 ሺህ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል ያሉት ኃላፊው፥ በተለይ ለተማሪዎች ምዝገባ ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማሩ ምቹ እንዲሆኑ ለማስቻል በክረምቱ ወራት ችግኝ የመትከል፣ የተጀመሩ ግንባታዎች የማጠናቀቅ፣ የመማሪያ ቁሳቁሶች የማሟላትና ሌሎችም ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ አህመድ ጀማል በልዩ ወረዳው የፍቃዶ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሲሆኑ በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል እንዲቻል በክረምት ወራት በትምህርት ቤቱ መምህራንና በበጎ ፍቃደኛ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም ከልዩ ወረዳው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ስልጠና እና የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡

አሁን ላይ በት/ቤቱ የተማሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መምህሩ፥ ትምህርት ቤቱን ለመማር ማስተማሩ ምቹ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ሶፊያ አለዊ እና አቶ አሰፋ ጎላ በልዩ ወረዳው በፍቃዶ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን በማስመዝገብ ላይ ሳሉ ካነጋገርናቸው የተማሪ ወላጆች መካከል ሲሆኑ፥ ልጆቻቸውን በወቅቱ ማስመዝገብ ከመቻላቸውም ባሻገር የተማሪዎች ውጤትን በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ተማሪ መይሙና እስማኤልና ፍርዶስ ጀሚል የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ሲሆኑ ለ2018 የትምህርት ዘመን በወቅቱ ከመመዝገባቸውም በተጨማሪ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ: ወለላ ኤልያስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን