የአምናው ጥፋት እንዳይደገም!

የአምናው ጥፋት እንዳይደገም!

በአለምሸት ግርማ

ጥራት ያለው ትምህርት ለስልጣኔ መሰረት ነው። እንዲሁም ፍትሐዊነትን ለማስፈንና ለዜጎች ጥራት ያለው አገልግሎት ለማግኘት ዋስትና ነው። የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ከሆኑት ተግባራት መካከል ደግሞ ፈተና(ምዘና) አንዱ ነው። ሀገራችን ባስቀመጠችው አዲስ መመሪያ መሰረት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በተለይም የ8ኛ፣ የ12ኛ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ መግቢያና መውጫ ፈተና ከቀድሞ በተሻለ ጥንቃቄ እንዲወስዱ እየተደረገ ይገኛል።

በዚህም መሰረት የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መውጫ ፈተና እንደሚሰጥ ማስታወቁ ይታወሳል። የመውጫ ፈተናው ተማሪዎች በተማሩባቸውና በሰለጠኑባቸው የሙያ ዘርፎች ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

ከዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተናው የሚዘጋጀው፣ የሚተገበረውና የሚተዳደረው በዩኒቨርሲቲዎች ሲሆን፤ ለዚህም ትግበራ ፖሊሲና ዝርዝር ማስፈጸሚያ መመሪያ መዘጋጀቱ ተገልጿል። የመውጫ ፈተናው በኦንላይን ለሁሉም የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህን የሚመጥን ዝግጅት እያከናወነ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል።

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመናበብ የመውጫ ፈተናውን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የመውጫ ፈተናውን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት አስፈላጊውን ግብዓት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

የመውጫ ፈተናው ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚጠበቅባቸውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት መያዛቸውን መለኪያ ነው። ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት አሰጣጥ ላይ ያሉበትን ሁኔታ በማሳየት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሚናው ከፍ ያለ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎን ተፈታኞችን በእውቀትና ስነ-ልቦና የማዘጋጀት ሥራ በመሰራት ላይ ሲሆን የመውጫ ፈተናው የውጤት ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥ ነው።

የመውጫ ፈተናው ለሁሉም የትምህርት ዓይነት ሲሰጥ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን ለተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ተደርጓል። እንዲሁም ድጋፍ የሚፈልጉ ተማሪዎች የመደገፍ ሥራ እየተሠራም ይገኛል። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናው በሚያተኩርባቸው የትምህርት ዓይነቶችን በመለየት የማጠናከሪያ ፕሮግራም እየተሰጠ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ብዙ ፈተናዎች ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። ከነዚህም መካከል የ8ኛ ክፍል እና የ12ኛ ክፍል ተጠቃሽ ናቸው። በደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅት አስተዳደርና የትምህርት ምዘና ጥራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረህይወት ሳልፎሬ የ8ኛና የ12ኛ ክፍል የፈተና ቅድመ ዝግጅቱን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፦

ፈተናን በሚመለከት ሀገር አቀፍ ስታንደርዱን የጠበቀ አሰራር ለመተግበር በዝግጅት ላይ እንገኛለን።

የ8ኛ ክፍል ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመስጠት ታስቦ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን ካለው አንዳንድ ጫና የተነሳ ክልሎች የየራሳቸውን መመዘኛ ፈተና እንዲያወጡ በተደረገው አሰራር መሰረት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛለን።

በዚህም መሰረት ቀድሞ 9 የትምህርት ዓይነቶች ፈተና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ዘንድሮ ግን 6 የትምህርት ዓይነቶችን ነው የሚፈተኑት። የሚፈተኑበትም ቦታ በከተማ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆን በገጠራማ አካባቢ ደግሞ በክላስተር ትምህርት ቤቶች ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነን።

እንዲሁም ቀድሞ 8ኛ ክፍሎችን የሚፈትኑት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የነበሩ ሲሆኑ አሁን ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ናቸው የሚፈትኗቸው። እጥረት ባለባቸው በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ዲግሪ ይዘው በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያስተማሩ ያሉ እና በቂ ልምድ ያላቸው መምህራን እንዲካተቱ በማድረግ እየተሰራ ነው። ይህም የተደረገው መምህራን ያስተማሯቸውን ተማሪዎች መፈተን የለባቸውም በሚለው መመሪያ መሰረት ነው።

የተፈታኝ ተማሪዎች ምዝገባን በተመለከተ ከዚህ በፊት በወረቀት ነበር የሚከናወነው። ወረቀቱም የሚገዛው ከውጭ ሀገር ነበር። ያንን ወጪ ለማስቀረት ዘንድሮ የ8ኛ ክፍል ተፈታኞች ምዝገባ በኦንላይን ተከናውኗል። መመዝገቢያ ሶፍት ዌሩም ቀድሞ ከውጭ ሀገራት ይገዛ የነበረ ሲሆን በዘንድሮው ግን እዚሁ ሀገር ውስጥ ማለትም 2014 ዓ.ም ኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ያዘጋጀው ስለነበር ከዚያ ነው የተጠቀምነው ብለዋል።

ይህም ወጪ ከመቆጠቡም በላይ ስራው ቀልጣፋ እንዲሆን አስችሎታል። የመፈተኛ ካርድም ከዚህ ቀደም ከሚደረገው በተለየ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤቶች እንዲያዘጋጁ ተደርጓል። በዚህም ከፍተኛ የሆነ የሀገር ሀብት ለማትረፍ ተችሏል።

የ12ኛ ክፍል ፈተናን በሚመለከት የተማሪዎች ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን ፈታኞቻቸውም የዩኒቨርሰቲ መምህራን ናቸው። ቀጣይ የሚጠብቀን ስራ ተማሪዎችን ወደ መፈተኛ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ማጓጓዝ ነው። ለዚህም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የምንሰራው ይሆናል።

ተማሪዎች ምን ዓይነት ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ሲናገሩ፦

ካለፈው ዓመት ብዙ ትምህርት መውሰድ ይቻላል። በነበረው ውጤት በክልላችን 180 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ መላክ አልቻሉም። ስለዚህ ወላጆች፣ ተማሪዎችና መምህራን ይህን ከግንዛቤ በማስገባት በቁጭት ሊሰሩ ይገባል።

ይህን ለማጠናከር ተማሪዎችን ለመደገፍ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ የማጠናከሪያ ድጋፍ እየተደረገም ሲሆን፤ በዚህም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት የማጠናከሪያ(የቱቶሪያል) ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል።

ለጉዳዩ በተሰጠው ትኩረት መሰረት መጋቢት ወር ላይ ወላይታ ዞን በመገኘት የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል። ያንን መድረክ እስከ ትምህርት ቤቶች እንዲወርዱ በማድረግ ተሰርቶበታል።

አቶ ገብረህይወት በሰጡን መረጃ መሰረት በክልሉ 128ሺ 163 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ይወስዳሉ። ከ8ኛ ክፍል ደግሞ 210ሺ 024 ተማሪዎች ለፈተና ተመዝግበዋል።

በዘንድሮው ዓመት በሚካሔደው የፈተና አሰጣጥ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች እንዲቀንሱ ወይም እንዳይደገሙ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል። ለዚህም የተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተባብሮ መስራት በእጅጉ ያስፈልጋል።

መንግስት እያደረገ ካለው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በተጨማሪ ተፈታኝ ተማሪዎች በቂ የስነ-ልቦና ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ራሳቸውን ከሚረብሹ ነገሮች በመጠበቅ ለፈተና መቅረብ መቻል አለባቸው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል!