የአስተሳሰብ ባህልና – ልማድ
በቦጋለ ወልዴ
“ህይወትህ በእጅህ ነው፤ መንገዱም ከፊትህ ነው” የሚለው ብርቱ ብሂል ያሰናዳው ዶ/ር ኤርሲዶ ሌንደቦ ስለ ህይወት እያንዳንዱ ሰው የራሱን ህይወት ቀራፂ መሆኑንም ያመላክተናል፡፡ “ኑሮ” የተሰኘችውና በ2013 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ለህትመት የበቃችው መጽሐፍንም ዋቢዬ አድርጌ ለህትመት ገፃችን ሳበቃት ከወዲሁ ከፍ ያለ አክብሮትን ለአዘጋጁና ለውድ አንባቢዎቻችን ይድረስ እላለሁኝ፡፡
ስላለፈው ታሪክና ስላለፈው የኑሮ ዘመን አንዳንዴ እናወራ የለ?… ዋናው ትኩረታችን ግን የዛሬውና የወደፊቱ ህይወታችን ነው፡፡ ዛሬ ምን እናድርግ ፣ ህይወታችን የብልፅግናና የደስታ እንድትሆን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ይሆን? ደግሞም ይህ ነው ዋናው ቁምነገር ሲል ከራሱ የተስማማ ተመስሏልም፡፡
አዎን! ያለፉት ጥረቶችና ስኬቶች ያኮራሉ፣ ግን ህይወትን በትዝታ መተካት የለብንም፡፡ ያለፉት ስህተቶችና ውድቀቶች ያስቆጫሉ፡፡ ግን ለወቀሳና ህይወትን በቁዘማ ለመተካት መሆን የለበትም፡፡
የትናንት ስህተቶችና ውድቀቶችም፣ ለዛሬው ለነገም የብቃት ማሻሻያ ትምህርት እንዲሁም የመነሳሳት ቁጭት እናድርጋቸው፡፡
ለምን? በየጊዜው የሚበለፅግ አስደሳች ህይወትን ለመቀዳጀት ነውና!
እውኑ ተፈጥሮ ግን በራሱ ጊዜ እውቀትና ምግብ አይሆንላቸውም፡፡
“እውን ተፈጥሮ የእጃቸውን ሰጣቸው” ያስብላል፡፡ እጃቸው ሥራ ስለፈታ የአንጐላቸውን ቅጣት ሰጣቸው ቢባልስ? አንጐላቸው ነዋ ሥራ የፈታው፡፡ ታዲያ እውኑ ተፈጥሮ፣ እጅግ ስሌት አዋቂና ፍትሃዊ ዳኛ አይመስልም? ግን ተፈጥሮ ነው፡፡ ስሌትና እውቀት ፍትህና ዳኝነት የሰው ሃላፊነትና ምርጫ ነው፡፡
ውሃ ቁልቁል መፍሰሱ ወደ በረዶነት መጠጠሩ፣ በሙቀት መትነኑ… በስሌት ወይም በስሜት፣ በእውቀት ወይም በዓላማ አይደለም፡፡ ማንንም ለማስተማርና እውቀት ለማስጨበጥ አልያም ማንንም ለመሸወድ አይደለም፡፡ ግራ ለማጋባትም አይደለም፡፡ አንዳችንን ለማስቀየም ወይም ሌላውን ለማስደሰትም አይደለም፡፡ በቃ! ተፈጥሮ ነው፡፡ የውሃ ቁልቁል መፍሰስ፣ ሲቀዘቅዝ መጠጠር ብሎም ሲሞቅና ሲፈላ መትነን ተፈጥሮ ነው፡፡
“ውሃ ቁልቁል የፈሰሰው በእውቀት ነው በስሜት?” “ለምን ዓላማ ምን አቅዶስ ፈሰሰ?” ተብሎ አይጠየቅም፡፡ ብንጠይቅም ምንም ፋይዳ አናገኝም፡፡ በራሱ ጊዜ አንዳች ሚስጥር እንዲነግረን አእምሮአችን ውስጥ እውቀት እንዲፈጥርልን ብንመኝ ከንቱ ምኞት ነው፡፡
ውሃ መትነኑ ተገቢ ምርጫ ነው? የሚደገፍ ተግባር ነው? ተብሎ አይመዘንም፡፡ “ሲበርድ የመጠጠር ባህርይ እንደ ብቃት ያስመሰግነዋል ወይም በድክመት ያስወቅሰዋል?” እንዲህ ዓይነት ተግባር መብት ነው ወይንስ ወንጀል? ብለንም አንዳኘውም፡፡
አእምሮአችን ከእውኑ ተፈጥሮ ጋር የሚኖረው ግንኙነት “እውነቱን በማስተዋል ላይ የተመሰረተ” ሊሆን ይገባል፡፡ “አዎ! ይኼ እውን ነው” የሚል አዎንታዊ ምላሽ ላይ የተመሰረተ አእምሮ እውነትን የያዘ አእምሮ ነው፡፡
አእምሮ በመጠቀም፣ እውነትን በማስተማር እና በማገናዘብ እውቀትን በቅጡ ያዳብራል፡፡ ስንል “አእምሮን መጠቀምና እውቀትን ማዳበር ይቻላል” ለማለት ብቻ ሳይሆን አእምሮን መጠቀምና እውቀትን ማዳበርም ይገባዋል” ከማለት ጋር መለያየት የለበትም፡፡ አዎ ይቻላል፡፡ አዎ አእምሮውን የመጠቀምና የማወቅ አቅም አለው፡፡ የሰው ተፈጥሮ ነው፡፡ ልክ እንደዚያው የመምረጥ አቅምም አለው፡፡ ይህም የሰው ተፈጥሮ ነው፡፡
የመጽሐፉ አዘጋጅ ዶ/ር ኤርሲዶ ሌንደቦ “ህይወትህ በእጅህ ነው መንገዱም ከፊት ነው” የሚለውን ወርቃማ እሳቤ እንደሚከተለውም በአፅኖት አስፍሮልናል።
1. አእምሮን ለመጠቀምና ተግቶ ለማወቅ መምረጥ ብሩህ የእውነት መንገድን መምረጥ ይቻላል፡፡ ወይንም ደግሞ “አእምሮን ላለመጠቀምና ከእውቀት ለመሸሽ መምረጥ” እውነት ላይ አምፆ ጨለማውን የጭፍንነት መንገድ መምረጥ ይቻላል፡፡
2. ለኑሮ በሚበጅ ዓለማ የጥረትና የሙያ አቅጣጫን መምረጥ የተቃና የሰኬት መንገድን መምረጥ ይቻላል፡፡ በተቃራኒው ለኑሮ የማይበጅ የማያዋጣና የማያዘልቅ የኪሳራ መንገድና /አቅጣጫን/ ገደላማ የውድቀት መንገድንም መምረጥ ይቻላል፡፡
3. ለሰው ተፈጥሮ የሚመጥን መልካምና ድንቅ የብቃት ስብዕናን የሚገነባ ክቡር የህይወት መንገድን አሊያም ለሰው የማይመጥንን ክፉኛ የተጣመመና ስብዕናን ከንቱ የሚያስቀር የጥፋት መንገድን መምረጥ ይቻላል፡፡
በዚህም ምክንያት ማንኛውንም የሰው ኃሳብ ንግግርና መረጃ በጭፍን ተቀብሎ ማፅደቅና ማስተጋባት ወይም በጭፍን ማስተባበልና ማጣጣል ተገቢ የማይሆነው፡፡
እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን መጠየቅና ከዕውኑ ተፈጥሮ ጋር በማመሰካከር ማረጋገጥ ትክክል ወይም ስህተት መሆኑን ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡
ማንኛውም የሰው ዓላማና ድርጊትም፣ በመንግስት የሚታወጅ ህግም ሆነ እቅድና ውሳኔ ፋይዳውና ተገቢነቱ ይመዘናል፡፡ በዘፈቀደ ሆ! ብሎ መደገፍና ሆ! ብሎ መቃወምም ተገቢ አይደለም፡፡ ዓላማው ይበጃል? ተግባሩ ያዋጣል? ምንና ማን? አሰራሩ ያዘልቃል? እንዴት? በሚሉ ጥያቄዎች አማካኝነት በምልዓት መመዘን አለበት፡፡
የማንኛውም ሰው ብቃትና ባህርይ፣ አልያም በማንኛውም አገር ውስጥ ጐልቶ የሚታይ አስተሳሰብና አኗኗር /ባህልና ልማድ/ የማንኛውም ተቋም አወቃቀር ስርዓትም … ይዳኛል፡፡ በጭፍን ማድነቅና መውደድ ወይም በጭፍን ማዋረድና ማጥላላት ተገቢ አይደለም፡፡
ቀሺም ወይም አሪፍ በብቃት የመጠቀ ወይም ከበቃት የራቀ፣ የሚደነቅና የሚከበር አሊያም በከፋት የረከሰና የወረደ ሊሆን ሰለሚችል በተገቢው የመዳኘት ቀና ፍትሃዊነት ያስፈልጋል፡፡
የዚህ ሁሉ መነሻውና መሠረቱ ደግሞ እውኑን ተፈጥሮ አስተውሎ “እውንነቱን በመገንዘብ የሚጀምር ብሩህ የእውነት መንገድ ነው፡፡
አእምሮአቸውን ተጠቅመው መማር፣ ማወቅና ማሰብ ለሚፈልጉ ዓላማ መያዝ ግብ መጨበጥና በፅናት መወሰንን ለሚመርጡ በተግባር መጣር፣ መስራትና መትጋት ለሚሹ ሰዎች ደግሞ እውኑ ተፈጥሮ ወለል ብሎ የተከፈተ የስኬት ጐዳና ነው፡፡
በእውኑ ተፈጥሮ ላይ የተመሰረተው ጥንቅራዊ አስተሳሰብ ውድቀትን ለማስወገድና ስኬትን ለመቀዳጀት የሚያስችሉ መሳሪያዎችን የሚያስታጥቁንም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
መሳሪያዎቹን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመመልከት ይበልጥ ከራሳችን ጋር ልናዋህዳቸውና ልንጠቀምባቸው እንችላለን ሲል ፀሐፊው በገሃዱ ዓለም የምናስተውላቸው የአስተሳሰብና የአኗኗራችን /ባህልና ልማድ/ በአስተውሎት ማነፅና መመስረት ጤናማ ህልውና ለትውልድ ይበጃል ማለቱ አይደል?! ቸር እንሰንብት፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ