“ትኩረት ያልተሰጣቸው ግጭቶች”

በፈረኦን ደበበ

የዓለም ማህበረሰብን ትኩረት የሚሰርቁ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ በሌላ በኩል አሳሳቢ መሆን የሚችሉ ችግሮች ብቅ ይላሉ፡፡ በዚህኛው ላይ ትኩረት ሲሰጥ አሁንም ሌላ ችግር በሌላ ጫፍ ላይ ያቆጠቁጣል፡፡

እንዲህ ውስብስብ የሆኑ ሁኔታዎች መፈጠር አቅምን ጭምር ያሳጣል። እያገባደድን ባለንበት የእኛው ዓመት ማህበረሰቦችን ሲፈታተኑ የቆዩ እንደ ሠላም እጦት፣ የኑሮ ውድነት፣ ድርቅና የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ትኩረትን በማሳጣት አንዳንድ ሀገራትና አካባቢዎችን የበለጠ ተጎጂ አድርጓቸዋል፡፡ ለትኩረቶች መነፈግም አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትን በመጥቀስ አፍሪካ ኒውስ የተባለው የመገናኛ ብዙሀን ያወጣው ዘገባም በእርግጥ ችግሮች መኖራቸውን ያመለክታል፡፡

“እጅግ ትኩረት የተነፈጋቸው 7 የአፍሪካ ሀገራት ዝርዝር” በሚል ርዕስ ያወጣው ዘገባ ተጎጂ የሆኑ ሀገራትን ሁሉ አሳይቷል። የደረሰበት ዓመተ-ምህረትና ለጉዳት የተዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥርንም ጠቅሷል፡፡

በሪፖርቱ ከተጠቀሱት ሀገራት መካከል የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቡርኪና ፋሶ ቅድሚያውን የምትወስድ ሲሆን ሁኔታውን በአካባቢው ከተንሰራፋው የአክራሪዎች ጥቃት ጋር ማገናኘቱም ሀገር ያወቀው ጸኃይ የሞቀው ያደርገዋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ወቅታዊ ያልሆኑ መረጃዎችን በማካተት የሀገራትን ቁጥር ያዘበራረቀና ከአፍሪካ ውጭ ያሉ ሀገራትን ሁሉ ቢጠቅስም፡፡

ቡርኪና ፋሶ እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ የእስላማዊ አክራሪዎች ጥቃት ሰለባ ሆና ቆይታለች በሚለው መንደርደሪያ ሀተታውን ሲጀምር ችግሩም በዓለም እጅግ ትኩረት ያላገኘው ሆኗል ብሏል የኖርዌይ ስደተኞች ም/ቤት የሚለውን የረድኤት ድርጅት በመጥቀስ።

ድርጅቱ በየዓመቱ ትኩረት ያልተሰጣቸው በሚል 10 የግጭት ተጎጂ ሀገራትን እንደሚያወጣ ጠቅሶ ለህዝብ መፈናቀል መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችንም ጠቁሟል፡፡ እነሱም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የፖለቲካ ተነሳሽነት ማጣት፣ የብዙሀን መገናኛዎች ሽፋን ማነስ እና የሰብአዊ እርዳታ ገንዘብ እጥረት እንደሆኑ በማስታወቅ፡፡

በድርጅቱ ሪፖርት መሠረት ቡርኪና ፋሶ ባለፈው ዓመት ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደነበረች አስታውቆ ይህም ቀደም ባሉ አምስት ዓመታት ከሞቱባት 14 ሺህ ሰዎች ጋር ይያያዛል ብሏል ከእነዚያ መካከል ግማሾቹ የሞቱት ደግሞ ከእ.ኤ.አ ጥር 2022 ወዲህ መሆኑን በማስታወቅ፡፡ ከ2 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች የውስጥ ስደተኞች መሆናቸውንም አሳይቷል፡፡

በዓመቱ የጨመሩ ግጭቶችና መፈናቀሎች ከአራቶቹ የሀገሪቱ ዜጎች አንዱን የሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ አድርጎታል መባሉንም ዘግቧል ከሚያስፈልገው ሰብአዊ የገንዘብ እርዳታ 42 በመቶ ብቻ መሠራጨቱን በማመልከት፡፡

ከተቋማት አንጻርም ሲታይ ሪፖርቱ በርካታ ጥቃቶች በውኃ ተቋማት ላይ እንደደረሱ አመልክቷል ብሏል በዚህ 830 ሺህ ሰዎች ውኃ እንዳጡና 6 ሺህ 200 ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ስላደረገ፡፡ በዚህ ምክንያት ከ1 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ትምህርት ማቋረጣቸውንም አስታውቋል፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው የፖለቲካ ያለመረጋጋት እራሱ የችግሩን ስፋት እንዴት አንደጨመረ ሲገልጽ በ2022 የተከሰቱ 2 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥታት መኖራቸውን ገልጿል፡፡

ቀጥሎ የተነተነው ስለ ሌላዋ የችግሩ ተጠቂ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ኮንጎ ሲሆን እሷም ካጋጠሟት ዘርፈ- ብዙ ቀውሶች አንጻር በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች ብሏል በተለይ በስተምሥራቅ ክፍሏ ከተከሰተው ቀውስ አንጻር፡፡

60 ዓመታትን የፈጀው የኮሎምቢያ ትጥቅ ትግል እራሱ ሀገሪቱን በሦስተኛ ደረጃ እንዳስቀመጣት ጭምር ገልጿል ሱዳንና ቨኔዙዌላን በማስከተል፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ብሩንዲ፣ ማሊ፣ ካመሩን፣ ኤልሳቫዶር እና ኢትዮጵያ ሲጨመር ቁጥሩ ወደ 10 እንደሚደርስ የጠቀሰው የመረጃ ምንጫችን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚፈጽመውን አድሏዊ አሠራርንም አውግዟል ብሏል በተለይ ለዩክሬን ይሰጥ የነበረውን ተመጣጣኝ ያልሆነ ድጋፍ በማስመልከት፡፡

የችግሩን ግዝፈት ለማሳየት ሪፖርቱ ተጨማሪ አመላካች ያስቀመጠ ሲሆን ይህንንም ለዩክሬን ከሚመደበው እያንዳንዱ ዶላር ጋር በማመሳከር አስቀምጧል፡፡ ከዚህ አንጻር ለዩክሬን ተብሎ ለሚወጣው እያንዳንዱ ዶላር በችግር ውስጥ ካሉ ሀገራት በሚወሰድ 25 ሳንቲም ይካካሳል ብሏል፡፡

ስለዚህ ትኩረት ያለመስጠት “እንደ ምርጫ” ቢሆንም ሊቀለበስ የሚችል ችግር ተብሎ ነው የተገለጸው፡፡

እነዚህና ሌሎች መረጃዎችን በምንመለከትበት ጊዜ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ማህበረሰብ ችግሮች በርካታ መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ ተፈጥሯዊም ሰው ሠራሽም፡፡ እያገባደድን በሚንገኘው ዓመት ያየነው ግን እነዚህ ተጽዕኖዎች በተናጠል ሳይሆን በአንድነት መከሰታቸውን ነው፡፡

ህዝቡ በፖለቲካና በማህበራዊ ጫናዎች የሚደርሰውን ችግር በአንድ በኩል ሲፋለም ተፈጥሮ በሌላ በኩል ጫና ይፈጥርባቸዋል። በተለይ በምሥራቅ አፍሪካና በሌሎች የዓለም አካባቢዎች ዘንድሮ የታየው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ችግሩን አወሳስቦታል። ከተከሰቱ የኃይል እጥረት እና ገንዘብ ቀውሶች ጎን ለጎን፡፡

የምዕራብ አፍሪካ ጉዳይ ሲታይ ደግሞ የበለጠ ውስብስብ ነው፡፡ የአሸባሪዎች ጥቃት በአንድ በኩል ሲኖር የፖለቲካ ቀውሱ እና ያለመረጋጋት በሌላ፡፡ ከእነዚህ መካከል በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ውጥረቶችን አስከትለዋል፡፡ የሚካሄደው የኃያላን መንግሥታት ፍጥጫም አንዲሁ፡፡

እንዲህ የዓለም ማህበረሰብ በብዙ ጠርዞች ለውጥረት ሲዳረጉ በየአካባቢው ትኩረት ያላገኙ በርካታ ተጎጂዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የተረሱና የተዘነጉ ማህበረሰቦችን በማውሳት የሚወጡ ሪፖርቶች ጉዳትና መንስኤዎችን ለማመልከት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።

የዓለም ማህበረሰብን ትኩረት የሰረቁ ሌሎች ሁነቶች በኃያላን መካከል እየተፋፋመ የመጣው የእርስ በርስ ጥርጣሬና የዚያ ውጤት የሆነው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ሲሆን ችግሩ ሀገራት አይናቸውን ወደ ግጭቱ እንዲያተኩሩ አድርጓል፡፡ ያለውን ሀብትና የሰው ኃይል ሁሉ ወስዶባቸዋል፡፡ ባደጉ ሀገራት ያሉ ዜጎችን ጭምር ለችግር ዳርጓል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንም ገለልተኛ የሆነ አቋሙን በማሳት በወገንተኛ የዓለም ፖለቲካ እንዲዘፈቅ አስገድዷል፡፡

ከእነዚህ ሁኔታዎች አንጻር ሪፖርቱን ያቀረበው የኖርዌይ በጎ አድራጎት ድርጅት ሰብአዊ እርዳታን ማቅረብ የሚገባው ከተጎጂ ማህበረሰቦች ፍላጎት እንጂ ከሀያላን ጂኦ-ፖለቲካ ፍላጎት ወይም ከብዙሀን መገናኛዎች የሚዲያ ሽፋን መሆን እንደለሌበት ያስጠነቀቀው ትክክለኛ ሆኖ ይወሰዳል፡፡