የጉራጌ ህዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ እና ሌሎች እሴቶችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለፀ
መምሪያው ከኪነ ጥበብ ማህበርና ክበባት ጋር በመተባበር “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ ያሰናዳው የኪነጥበብ ዝግጅት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ በመርሃ ግብሩ ተገኝተው እንዳሉት፤ የዞኑ አስተዳደር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመርዳት የበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
የጉራጌ ማህበረሰብ አካባቢውን በማጽዳት የካበተ ልምድ ያለው በመሆኑ ከተሞች ከዚህ መማር አለባቸው ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘርፉ አርአያነት ያላቸው ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አንስተዋል።
በዞኑ የተጀመሩ የመረዳዳት በጎ እሴቶችን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኃላፊው አስገንዝበዋል።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተቋሙ የጉራጌ ህዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ እና ሌሎች እሴቶች ከማልማትና ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን ማህበረሰቡ የሚያከናውናቸው በጎ ተግባራት ይበልጥ እንዲጎለብቱ በኪነጥበብ የተደገፉ የግንዛቤ ማጎልበቻ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የጉራጌ ማህበረሰብ በባህላዊ አውራ ጎዳናዎች “ጀፎረ” ያካበታቸውን መልካም ልምዶችን ተግባራዊ በማድረግ ምቹ እና ማራኪ ከተሞች ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል ወይዘሮ መሠረት።
አንባቢ ትውልድ ሚዛናዊና ምክንያታዊ ዜጋ የመሆን እድሉ ከፍ ያለ ነው ያሉት የመምሪያ ሀላፊዋ፤ በወልቂጤ ከተማ የንባብ ሳምንት በከተማው የጎዳና ላይ ቤተ መፅሀፍት ማስጀመራቸውን ጠቁመዋል።
መጽሐፍትን የማንበብ ለሌሎች ገዝቶ የመስጠትና አሰባስቦ ለበጎ አላማ የማዋል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
ኪነጥበብ የአንድን ማህበረሰብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ እና ሌሎች እሴቶች የሚተዋወቁበት፣ ለትውልድ የሚሸጋገርበት አንዱ መንገድ ነው ያሉት ወይዘሮ መሰረት፤ በዚህም ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች እና ግለሰቦችን ለማበረታታት የመሰል መድረኮች ፋይዳ ጉልህ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል ሃላፊዋ።
ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል በሰጡት አስተያየት፤ የኪነ ጥበብ ስራዎች የማህበረሰቡ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ለማወቅና ለማስተዋወቅ እንዲሁም አንድነትን ለማጠናከር ያላቸው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ በዘርፉ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
አክለውም በዘርፋ ባለተሰጥኦዎችን ለማበረታታትና ለማፍራት መሰል መድረኮች ሚናቸው የጎላ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የወልቂጤ ከተማ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ታደለ በቀለን ጨምሮ ሌሎች የዞንና የከተማ እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት ቤት ቀርበዉ እንዲመዘገቡ ወላጆች የሚጠበቅባቸዉን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
የተጀመሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሀዲያ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ተናገሩ
በሆሳዕና ከተማ እየተገነባ ያለውን የመንገድና የኮሪደር ልማት ስራ በታቀደው ጊዜ በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ