የሀገር ባለውለታ የሆኑት አረጋውያን እና አቅመ ደካማ ወገኖች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር ገለፀ
በከተማው ባለሀብቶችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሰተባበር የአረጋውያን ቤት ግንባታና እድሳት መርሀ ግብር ተከናውኗል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለፁት፤ የሀገር ባለውለታ የሆኑት አቅመ ደካሞች እና አረጋውያን ትርጉም ባለው መልኩ እንዲጠቀሙ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በከተማው በወጣት ባለሃብቶችና በሌሎችም በኩል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያየ መንገድ እገዛ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም አቅመ ደካሞች እና አረጋውያንን የመደገፍ እንዲሁም ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዛሬው እለትም በከተማው የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዚሁ አካል መሆኑንና በቀጣይም ይህ በጎ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
መንግስት ሰው ተኮር ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነ የገለፁት አቶ ሙራድ፤ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት አማካይነት የአረጋውያን ቤት መገንባትና መጠገን የብዙዎችን ህይወት የሚቀይር ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አብራርተዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ተደለ በቀለ በበኩላቸው፤ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋዊያን ተጠቃሚ ለማድረግ በከተማው ሁሉንም ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰሩ ተግባራት መካከል አንዱ ሰው ተኮር ስራ መሆኑን በማንሳት በዚህም በከተማው በርካታ ወጣቶችንና ባለሀብቶችን በማሰተባበር አበረታች ስራ እየተከናወነ በመሆኑ ተግበሩ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
አረጋዊያን የህብረተሰቡ ማህበራዊ የአኗኗር ስርአት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ስላላቸው በቂ ድጋፍና እንክብካቤ ሊደረግላቸው አንደሚገባ በማመላከት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ማህበረሰቡ ባህል ሊያደርገው እንደሚገባ ገልፀዋል።
የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስራት ታደለ፤ በከተማው በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ14 ዘርፎች ከ27 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል፣ 122 ዩኒት ደም የመለገስ፣ አልባሳት የማሰባሰብና ማዕድ የማጋራት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 48 ሺህ 275 የሚሆኑ የከተማው የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በመግለፅ በዚህም እስካሁን ባለው ሂደት በተከናወኑ ተግባራት 18 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን መቻሉን ጠቅሰው ተግባሩ በቀጣይም ሁሉንም ማህበረሰብ በማሳተፍ እንደሚከናወን አብራርተዋል።
በከተማው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ባለሀብት ፋሩቅ ተሰማ በሰጠው አስተያየት፤ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሰማራት በየዓመቱ የአረጋውያን ቤት ግንባታና ጥገና በማድረግ የራሱን አሻራ እያስቀመጠ እንደሆነ ተናግሯል።
ለአቅመ ደካሞች የሚያደርገው ድጋፍ የሚሰጠው የአእምሮ እርካታ ጥልቅ እንደሆነ የገለፀው ባለሀብቱ በቀጣይም ድጋፍን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
ቤቱ እየተገነባላቸው ከሚገኙ አረጋዊያን መካከል በሰጡት አሰተያየት፤ ከዚህ ቀደም በችግር ውስጥ ሆነው ኑሮአቸውን እየገፉ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን በተደረገላቸው ድጋፍ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት ቤት ቀርበዉ እንዲመዘገቡ ወላጆች የሚጠበቅባቸዉን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
የተጀመሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሀዲያ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ተናገሩ
በሆሳዕና ከተማ እየተገነባ ያለውን የመንገድና የኮሪደር ልማት ስራ በታቀደው ጊዜ በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ