የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ111ሺህ በላይ የኩነት ምዝገባዎችን ማከናወኑን አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ ከ111ሺህ 600 በላይ የኩነት ምዝገባዎችን ማከናወኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ቅንጅታዊ ሥራ በዘርፉ ላይ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ጉልህ ሚና እንደነበረው ተመልክቷል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ከበደ ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሆሳዕና ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፥ መሥሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ማከናወኑን አብራርተዋል።
ሁሉም ዜጋ የሚታወቅበትን ኢትዮጵያ እንፍጠር በሚል ራዕይ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኘው ኤጀንሲው፥ ዜጎች በኩነት ምዝገባ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
በመሆኑም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም የምዝገባ ዘርፎች በልደት፣ በጋብቻ፣ ፍቺ፣ በጉድፈቻና በሞት የምዝገባ ሽፋን በመስጠት የዕቅዱን 97.7 በመቶ ማሳካት ስለመቻሉ አቶ አበበ ጠቁመዋል።
በክልሉ ከሚገኙ ከ1ሺህ 274 ቀበሌያት የኩነት ምዝገባ ሥራውን በ1ሺህ 248 ቀበሌያት ተደራሽ በማድረግ ዜጎች አገልግሎቱን በተገቢው እንዲያገኙ የማስቻል ሥራ መከናወኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል ።
አቶ አበበ አክለውም ለውጤታማነቱ ጠንካራ የድጋፍና ክትትል እንድሁም የጤና፣ የትምህርት፣ የሚዲያና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበርም አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ጉድለቶችን በመለየት እርምት እንደሚደረግ አመላክተዋል።
በተቋሙ የሚስተዋሉ የግብዓት እጥረት፣ የሠው ኃይል ውስንነት፣ ብልሹ አሠራሮችንና የመረጃ ልውውጥ መቀዛቀዝና ሌሎች መሰል ችግሮች መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ችግሮቹን ለመቅረፍ እጀንሲው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አቶ አበበ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: አብዱልሰመድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
አሊያንስ ኮሌጅ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን በማፍራት የሀገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታወቀ
በ2018 የትምህርት ዘመን ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመጡ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረዉ መቀጠል ይኖርባቸዋል – የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻዉ ከበደ
ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት ቤት ቀርበዉ እንዲመዘገቡ ወላጆች የሚጠበቅባቸዉን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ