ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የቦረዳ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት አስታወቀ

ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የቦረዳ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጋሞ ዞን የቦረዳ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
‎‎
‎ወ/ሮ ካሰች ክብረት ሥራው ድንቅ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ አምራች ማህበር ሰብሳቢ ሲሆኑ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ እንዲቻል ጂ.አይ.ዜድ የተሰኘ ድርጅት በማገዶ ቁጠባ ምድጃ ዙሪያ በሀላባ ስልጠና እንዲወስዱ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
‎
‎ቪታ የተሰኘ ድርጅት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የገበያ ትስስር መፍጠር በመቻሉ ለተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች እያቀረብን እንገኛለን ያሉት የማህበሩ ሰብሳቢ ወ/ሮ ካሠች፥ 15 ሺህ 300 ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ለገበያ ማቅረብ በመቻላቸው ከ6 ሚሊየን 850 ሺህ ብር ካፒታል እንዲያገኙ አመላክተዋል።
‎
‎ማህበሩ አስር ለሚሆኑ ሥራ አጦች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
‎
‎ወ/ሮ ዘመቱ ተሾመ የማህበሩ አባል በመሆናቸውና ወደ ሥራ በመግባታቸው የወንድን እጅ ከመጠበቅ እንዳዳናቸው አስረድተው ከሚያገኙት ገቢ ፍየል ገዝተው እያረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
‎
‎ሌላኛዋ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወ/ሮ ጤና አበራ በየቤቱ በመሄድ ምድጃውን መገጣጠም በመቻላቸው ተጠቃሚ እንደሆኑ አስረድተዋል።
‎
‎የቦረዳ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አማረች አይዛ ሴቶች የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑ ሥራዎች በትኩረት እየተሰራ መሆናቸውን ተናግረዋል።
‎
‎ሴቶች በማህበር ተደራጅተው ቁጠባ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይደረጋል ያሉት ኃላፊዋ ከማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ማህበር በተጨማሪ በጓሮ አትክልትና በዶሮ እርባታ ላይ እንዲያተኩሩ ይደረጋል ነው ያሉት።
‎
‎በቦረዳ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት የሴቶች ንቅናቄ ተሣትፎ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ኢሳያስ ኮይራእ በወረዳው ባሉ 31 ቀበሌያት የሚገኙ 17 ሺህ 586 ሥራ አጥ ሴቶች በማህር በመደራጀት በገቢ ማስገኛ ሥራ እንዲሰማሩ ተደርጓል።
‎
‎ለአብነትም በማገዶ ቆጣቢ ምድጃ የተደራጁ ሴቶች ወደ አጎራባች ዞኖችም ጭምር ምርታቸውን እንዲያቀርቡ በመደረጉ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክተዋል።
‎
‎ዘጋቢ ፡ ታምሩ በልሁ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን