የደላሎች አሻጥር ሲፈተሽ
በደረሰ አስፋው
በአዲሱ የንግድ አዋጅ የድለላ ስራ የሚስራ ሰው በግልጽ “ነጋዴ” እንደሚባል ይገልጻል። በመሆኑም የንግድ ፍቃድ የማውጣት እና ይህን ተከትሎም የሚመጡ ግዴታዎችን መወጣት አለባቸው። ነገር ግን በአብዛኛው የሀገራችን ከተሞች የሚገኙ ደላሎች ከጥቂቶች በስተቀር ንግድ ፍቃድ ሲያወጡም ሆነ ግብር ሲከፍሉ አይታይም። ይባስ ብሎ ግን በድለላ ስራቸው የሚሰሩት አሻጥር ሀይ ባይ ያጣ መሆኑ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡
“ይሁኔ” የሚል ስም አላቸው፡፡ ለበርካታ ምግብና የመጠጥ ቤቶችም መድመቂያ ናቸው። እነዚህ ማናቸው ካላችሁ ደላላዎች ናቸው፡፡ ችግር በአጠገባቸው ያለፈም አይመስሉም፡፡ ሁሉም ነገር ይሁን እንጂ መከራከር የለም በማለት ይታማሉ። ይህም ይመስለኛል “ይሁኔ” የሚል የዳቦ ስም ያሰጣቸው፡፡
የድለላ ስራ አድካሚ ያልሆነ፣ ኪሳራም የሌለበትና ዳጎስ ያለ ገቢን የሚያስገኝ በመሆኑ የደላሎች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል። በአንዳንድ ከተሞች ሀዋሳን ጨምሮ ከመብዛታቸው የተነሳ ከሻጩና ገዥው ቁጥር ሊስተካከሉ የቀራቸው የለም እየተባለም በስፋት ይነገራል፡፡
በአሁኑ ወቅት የነዚህ ሰዎች ተጽእኗቸውም እንዲሁ የዋዛ አይደለም፡፡ በግብይት ሥርዓት ውስጥም የድለላ ሥራ ተፅዕኖው እየጎላ መጥቷል። ገበያው በነዚህ አካላት መዳፍ ውስጥ ገብቷል።
አለያም በነሱ ቁጥጥር ውስጥ ወድቋል፡፡ የድለላ ሥራ ወትሮ ቤት፣ መኪናና ቦታ የመሳሰሉትን ንብረቶች በማሻሻጥና በማከራየት ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ዛሬ የምናየውን ዓይነት ተፅዕኖ ፈጣሪነትም የምንመለከትባቸው አልነበሩም፡፡
“ደላላ” የሚለው ስያሜ ከዚህ በተለየ ተግባር የሚገለጽ እየሆነ ነው፡፡ እንደቀድሞ ይታወቁበት በነበረው አሠራራቸው ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን አድማሳቸው ሰፍቶ ጡንቻቸው ፈርጥሞ በግብይት ሥርዓት ውስጥ “ሁነኛ” ሥፍራ እየያዙም ነው። ገበያውን የማሽከርከር አቅም ፈጥረዋል። የመንግስት የስራ ሀላፊዎችን እጅ የመጠምዘዝ ሀይላቸውም እንዲሁ፡፡
ድለላ ያልገባበት ቦታ እንደሌለ ይታወቃል። ለግብይት ሥርዓቱ ጠንቅ የመሆናቸው ጉዳይም የዚያኑ ያህል እያደገ መሄዱን በግልጽ እየተመለከትን ነው፡፡ ችግሩ የኅብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ራስ ምታት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በተለያዩ አገልግሎቶች ውስጥ ያላቸው ሚና ለመልካም አስተዳደር ሥጋት መሆናቸውም አልቀረም፡፡ ለማሳያነት ትንሿን የቤት ኪራይን ወይም ተከራይና አከራይን በማገናኘት ዙሪያ ያለውን እንመልከት፡፡ ይህን ስላችሁ ከሰማሁት ብቻ ሳይሆን ከተመለከትኩት አልፎ ተርፎም በራሴ ከደረሰብኝ በመነሳትም ጭምር ነው፡፡
በየዕለቱ ተከራይና አከራይን የሚያገናኙት እነዚህ አካላት ከአከራዩ ዕውቅና ውጭ ዋጋ የመወሰን ኃይል ይዘዋል፡፡ ቀድሞ ሻጭና አከራይን አገናኝተው ኮሚሽን ተቀብለው ብቻ ዞር የሚሉ ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን ከዚህ በተለየ እየተንቀሳቀሱ ነው የሚገኙት፡፡ ሻጭ ከሚያገኘው በላይ ዳጎስ ያለ ረብጣ ብር በማግኘት የገቢ ምንጫቸው እያደገ ይገኛል ፈርቅ በሚሉት፡፡
በሰሞኑን በቤት ማሻሻጥ ስራ የተሰማራው ደላላ የፈጸመውን አሻጥር ስመለከት አግራሞትን ፈጥሮብኛል፡፡ ለዛውም አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡- ደላላው ለሻጩ አንተ ይህን ያህል ብር ትቀበላለህ፡፡ በዉሉ ላይ ግን በዚህን ያህል ብር ትፈርማለህ በማለት ከሻጩ ጋር ይሰማማል፡፡ ባለቤቱ ታማበት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለመውሰድ በጭንቅ ውስጥ ያለው የቤት ሻጭ ግን ለዚህ ሚስጥራዊ ስምምነት አላቅማማም፡፡ ለጊዜው እንዲሸጥለት እንጂ ሌላ ንትርክ ውስጥ መግባትን አልፈለገም፡፡ የሱ ሀሳቡ የባለቤቱን ህይወት ለማትረፍ እንጂ፡፡
ቀድሞ ከቤት ሻጩ ጋር የተነጋገረው ደላላም በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለማሻሻጥ ተስማምተዋል። ገዥው ቀርቦ ገንዘብ ከተለዋወጡ በኋላ በውሉ ላይ የተመለከትኩት ቤቱ የተሸጠው በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሳይሆን በ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ነው፡፡ ደላላው 2 መቶ ሺህ ብር ቅርጥፍ አድርጎ እንደበላ ተረዳሁ፡፡ ድለላው የሚያገኘው 2 በመቶ የኮሚሽን ክፍያ ሳይጨመር ማለቴ ነው፡፡ በዚህ መቆጨቴ አልቀረም በቅርብ የነበሩ ሰዎችም አፍ አፌን አሉኝ፡፡ ይሄን ብር ትልቅ ማድረግህ ነው? ይሄ እንዲያውም ትንሽ ነው ብለውኝ አረፉ፡፡
እንደቀድሞ የቤት አከራይም ቤቴን የማከራየው በዚህን ያህል ዋጋ ነው ብሎ ለመናገር የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ንብረቱ የአከራዩ ቢሆንም ያዋጣኛል ብሎ ዋጋ መተመን ግን አይችልም፡፡ ደላሎች በሚተምኑለት ዋጋ ብቻ ነው ጨዋታው እየሆነ ያለው፡፡ በየጊዜው ለቤት ኪራይ ዋጋ መናር ቀዳሚ ምክንያት ሌላ ምንም ምክንያት የለም፤ የሆድ አደሮች ህሊና ቢስነት ስራ እንጂ፡፡ ለቤት ኪራይ እጥረትም እንደሰበብ የሚወሰደው ይኸው ልጓም ያጣው የደላሎች የፈረጠመ ጉልበት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
ዋጋ መወሰናቸው ሳያንስ ቤቱ ከተከራየ በኋላም አከራዮቹን በመጠምዘዝ የሚሠሩት ያልተገባ ተግባር የድለላ ሥራን የተለየ መንገድ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ 4 ሺህ ብር እንዲከራይ ያደረጉትን አንድ ቤት ከሦስት ወራት በኋላ 5 ሺህ ብር አከራየዋለሁ ብለው ባለቤቱን በመጠምዘዝ የሚፈጥሩት ሸፍጥ አማራሪ ብቻ ሳይሆን አደገኛ እየሆነ መጥቷል፡፡
የቤት ኪራይ ለአንድ ወር መከፈሉ ቀርቶ የስድስት ወርና ከዚያም በላይ መሆን እንዳለበት የሚደነግጉትም እነዚሁ አካላት ናቸው። የወር ደመወዝተኛ የስድስት ወር ካልከፈለ ቤት ለማግኘት የማይችል መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ተመልክቻለሁ፡፡ ይሄው እጣ ፈንታ እኔም ስለገጠመኝ ሌላ እማኝ ልጠቅስም አልዳዳሁ። ጥቂት የማይባሉ አከራዮችም አልጠግብ ባይነት ከደላሎቹ ያልተናነሰ በደል እየፈጸሙ ነው፡፡ የቤት አከራዮች ለደላሎቹ ፀያፍ ተግባር ተባባሪ ባይሆኑ እንዲህ ያለው ተግባር እንደማይስፋፋ መረዳት አያዳግትም፡፡
ዛሬ ለመልካም አስተዳደር ፀር ስለመሆኑ እየተነገረ ያለው የመሬት ዋጋ መናርም ደላሎች ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ለመታዘብም ችያለሁ፡፡ በቦታ ሽያጭ ዙሪያ ቢሆን ከባለ ቦታው ዕውቅና ውጭ የሚፈጸም ነው፡፡ መች መሸጥ እንዳለበትና አንዳንዴም ለማን ሊሸጠው እንደሚገባ የሚወስኑትም እነሱ ናቸው፡፡ ለሌሎች ተገልጋዮች ፍዳ የሚሆነው የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጉዳይ ማስፈጸም፣ ካርታ ማዘጋጀትና የመሳሰሉት ጉዳዮች ለነሱ ክፍት የመሆኑ ጉዳይም የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል፡፡
የቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ሌሎችም ምርቶች ግብይት ሳይቀር እየተሠራ ያለው በደላሎች ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በገበያ ቅብብሎሽ መሀል ያላቸው ሚና ተደራራቢ ነው። ከምርቱ መነሻ በብዙ እጥፍ አድጎ ለመከረኛው ሸማች ሲደርስ ዋጋው ሰማይ ይሰቀላል፡፡ ታዲያ በነዚህ መሃል ያለው ደሃው በምን አቅሙ ይቻለው? በምርቶች ዝውውር እነሱን ሊጠቅም ያልቻለ ግብይት ካለ ምርቱን በመያዝ ወይም እስከማሰባሰብ ድረስ ይሄዳሉ፡፡ በቀጣይም እጥረት በመፍጠር ገበያ ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ ደላሎች እጀ ረጅም ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች የተሰወረ አይደለም፡፡ ግን ማን ይንካቸው፡፡ ሁሉም የጥቅሙ ተጋሪ ነውና አይቶ እንዳለየ ሰምቶ እንዳልሰማ እየተሆነ ያው አለን፡፡
እንደ ማሳያ የቀረቡት እነዚህ ጥቂት ጉዳዮች አዲስ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ችግር ከመስተካከል ይልቅ እየተስፋፋ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ የችግሩን ግዝፈት ያህል መፍትሔው ላይ እየተሠራ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ደላሎች አደጋ እየሆኑ ነው የሚለው አባባል ከመንግሥት ተደጋጋሚ የተነሳ ቢሆንም፣ ስለተወሰደው ዕርምጃ ግን የሰማነውም ሆነ ያየነው ነገር ያለመኖሩ ለምን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
ይህን ለማለት የወደድነው እንዲሁ በዋዛ አይደለም፡፡ ከድለላ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ሥርዓትና ደንብ ሊኖራቸው ይገባል ለማለት እንጂ፡፡ አብዛኛው አሠራር ከራስ ጥቅም ጋር የተሳሰረ እየሆነ መሄዱ ችግሩን አጉልቶታል። የግብይት ሥርዓቱ መላ ሊፈለግለት ካልተገባ ገበያው ምንም እሴት በማይጨምሩ ጥቂቶች እጅ ወድቆ የባሰ ትርምስ እንዳይፈጠር ፍርሃትም ሆነ ስጋት ስላደረብኝ ነው፡፡ ከድለላ ሥራ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎች በሕግ ሊደገፉ፣ ሥርዓትና ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው መሠራት አለበት፡፡ በሕጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱም በማድረግ ኅብረተሰቡን ከችግር መታደግ ያስፈልጋል፡፡
እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግልፅ ባይሆንም የፍቅር ወይም የትዳር አጋርም እናገናኛለን የሚሉ ማስታወቂያዎችን ተመልክቻለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እህል፣ ከብት፣ ወርቅ፣ ቡናና ሲሚንቶ በመሳሰሉ የሸቀጦች ግብይት ላይ ዋጋ እስከ መወሰን ደርሰዋል። በየሰፈሩ ያሉ ትንንሽ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች፣ የስልክ እና የመብራት ቋሚ ምሶሶዎች ላይ የድለላ ማስታወቂያ በብዛት ይታያል። አሁን አሁን ደግሞ በማህበራዊ ትስስር ገፆች ጭምር የድለላ ማስታወቂያ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ይህ ግን ለህዝቡ ጥቅም ጠብ የሚል ነገር የሚያበረክቱ ቢሆን እሰየው ነበር፡፡
ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርም በነዚሁ ደላሎች መዳፍ ላይ ወድቋል፡፡ ያልተጨበጠ ተስፋ በማቅረብ ብዙዎችን ለችግር እያጋለጡ እንደሆነ እየተመለከትን ነው፡፡ በርካታ ወገኖች ካሰቡት ሳይሆን ካላሰቡት ችግር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ ተስፋቸው መና ቀርቶ የህይወታቸው እጣ ፋንታ ተበላሽቶ ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ በሚደርስባቸው ስቃይ የተነሳ ለመመለስ ቢያስቡም እንኳ እድሉን ማግኘት አይችሉም፡፡ በበረሃ ”ረሃብና ጥም፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ድብደባ፣ ዘረፋና ሌሎች ጥቃቶች እየደረሰባቸው ነው።
ምንም ዓይነት ግብር የማይከፍሉት ደላሎች በመቶ ሺዎች የሚገመት የኮሚሽን ክፍያ ቢያገኙም ለመንግስት ግን ከሚያገኙት እንኳን ግብር የሚከፍሉ አለመሆናቸው ደግሞ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር የንግድ ፈቃድ እንኳ የላቸውም፡፡ በድለላ ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች ግብር እንዲከፍሉ የሚያስችል የአፈፃፀም መመሪያ ቢዘጋጅም ይህን ግን ተከታትሎ የሚያስፈጽም አካል ግን የለም፡፡
ማንኛውም ሻጭ ወይም ገዥ እንዲሁም አከራይ ወይም ተከራይ የድለላ ክፍያ የሚፈፅመው ደላላው ህጋዊ ንግድ ፍቃድ እና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ካለው ብቻ መሆን አለበት። ይህም የድለላ ባለሙያዎችን ወደ ህጋዊ የአስራር መስመር በማስገባት መንግስትና ህዝብ ከአገልግሎት ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ያስገኛል፡፡ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ለሌለው ደላላ ክፍያ መፈጽም የሚያስቀጣ መሆንም አለበት ለማለት እንወዳለን፡፡
More Stories
“ኩርፊያ እና ንትርክ አልወድም” – ጋዜጠኛ ገናናው ለማ
በ2030 ደህንነቱ የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ለሁሉም
ኮንፈረንስ ቱሪዝም