የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ

የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ

በልዩ ወረዳው በተደራጁ ማህበራት በኩል በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረውን የማምረቻና መሻጫ ሼድ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሼድ ግንባታ ተጠናቆ ለማህበራት ለማስተላለፍ ዝግጁ መሆኑም ተጠቁሟል።

መንግስት እንደሃገር የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም ከፍ በማድረግ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እያደረገ እንዳለ ይነገራል።

በቀቤና ልዩ ወረዳም በርካታ ዜጎች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ በማደራጀት ውጤታማ አንዲሆኑ እየተሰራ ይገኛል።

በልዩ ወረዳው ካሉ ማህበራት መካከል በሰብር የብረታብረትና እንጨት ስራ ዮሲሲ የባህላዊ አልባሳት አምራች ማህበራት ተጠቃሾች ናቸው።

ወ/ሮ ሙኒራ ሰይድ የዮሲሲ የባህላዊ አልባሳት አምራች ማህበርና ወጣት ማረፍ ሱልጣን ደግሞ የበሰብር የብረታብረትና እንጨት ስራ ማህበራት አባል ናቸው።

አባላቱ ታዲያ ተደራጅቶ መስራት በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንደሚያደርግ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሰረት በማህበር በመደራጀት ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፀው በዚህም ውጤታማ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል።

ስራን ከመናቅና ከማማረጥ በመውጣት ሌሎች ስራ አጥ ወገኖችም መንግስት ያመቻቸውን እድል ተጠቅመው በመረጡት ዘርፍ ተደራጅተው በመስራት ከጠባቂነት መላቀቅ ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

አቶ ቶፊቅ ሃዲ የዮሲሲ የባህላዊ አልባሳት አምራች ማህበሩ ሰብሳቢ ሲሆን ማህበሩ በ2017 ዓ.ም በአራት የቤተሰብ አባላትና በጥቂት ካፒታል ስራ መጀመሩን ገልፆ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ተናግሯል።

በተለይም በልዩ ወረዳው በመሰል ዘርፍ የተደራጁ ማህበራት ባለመኖራቸው ዮሲሲ ግን በአጭር ጊዜ ምርቶቹ እንዲተዋወቁለትና የገበያ እድልም እንደፈጠረለት ነው ያብራሩት ሰብሳቢው።

ወጣት ሰባሁዲን ጀማል ደግሞ የበሰብር የብረታብረትና እንጨት ስራ ማህበር ሰብሳቢ ነው ማህበራቸው በ2009 ዓ.ም በአምስት አባላትና በ70 ሺህ ብር ካፒታል ስራ ወደስራ መግባቱን አስታውሶ አሁን ላይ ካፒታላቸው 900 ሺህ መድረሱንም ተናግሯል።

በተጨማሪም ይላል ሰብሳቢው ከማህበሩ አባላት ባሻገር ለሌሎችም ስራ አጥ ወገኖች በቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩንም አመለክቷል።

ከስልጠና፣ ከገበያ ትስርርና ከሌሎች ድጋፍ ክትትሎች አኳያ በልዩ ወረዳው በኩል የሚሰራው ተግባር ይበል የሚያሰኝ መሆኑን የገለፁት ሰብሳቢዎቹ፤ ይሁን እንጂ አሁን ካሉበት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑና በምርቶቻቸው ለአካባቢ ብሎም ለሃገር እንዲተርፉ የመስሪያና መሸጫ ሼድ እጦት እክል እንደሆነባቸው ነው ያብራሩት።

በመሆኑም ይህ ችግር እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብዱል ሃሚድ አስፋው፤ መንግስት የወጣቱን የስራ እድል የመፍጠር ጉዳይ ከዳቦ በላይ አድርጎ በማየት ልዩ ወረዳው የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

በመሆኑም በልዩ ወረዳው በተደራጁ ማህበራት በኩል ከዚያ ቀደም በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረውን የማምረቻና መሻጫ ሼድ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሼድ ግንባታ ተጠናቆ ለማህበራት ለማስተላለፍ ዝግጁ መሆኑንም አቶ አብዱል ሃሚድ አብራርተዋል።

ከነበረው በተሻለ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና የብድር አቅርቦቱንም አማራጭ ለማስፋት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ በመስራት በቀጣይ ለበለጠ ውጤታማነት እንሰራለንም ብለዋል ሃላፊው።

ሌሎች ወደ ስራ ያልገቡ ስራ አጥ ወጣቶች በመረጡት የስራ ዘርፍ በመደራጀት መንግስት ያመቻቸላቸውን እድል በተገቢው ቢጠቀሙት ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰብ ብሎም ለሃገር መትረፍ የሚችሉበት ተግባር ለማከናወን ጽ/ቤቱ ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን