የሀላሊ መጀመሪያ ጀረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች በአገልግሎት አሰጣጡ መደስታቸውን ገለጹ

የሀላሊ መጀመሪያ ጀረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች በአገልግሎት አሰጣጡ መደስታቸውን ገለጹ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ የሀላሊ መጀመሪያ ጀረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች በአገልግሎት አሰጣጥ መደስታቸውን ተናገሩ፡፡

የተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ተገማች፣ የሚለካ እና ተገልጋይ ተኮር እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን ሆስፒታሉ አስታውቋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የግል አስተያየታቸውን ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከሰጡ ተገልጋዮች መካከል አቶ ኤርሚያስ ሔንጄራ እና ወይዘሮ አልማዝ ሹቴ በወረዳው የቦሣ ማንአራ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ፥ በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የሀላሊ 01 ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው ወይዘሮ ፈለቀች ማዳ፥ ከሆስፒታሉ ባለሙያዎች በኩል በተደረገላት እንክብካቤና ቀልጣፋ አገልግሎት ደስተኛ ስለመሆኗን ገልፃለች።

ሆስፒታሉ ከቅርበቱም በላይ በዋጋውም ተመራጭ መሆኑን እና ስትደርስ የገጠማት አገልግሎት አሰጣጥ ከዚህ በፊቱ የተለየ መሆኑን አመላክታለች፡፡

በሆስፒታሉ ከአገልግሎት አሰጣጥ ከመድኃኒትና ክህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በፊት ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎች እየተፈታ መምጣቱን ተገልጋዮች ተናግረዋል።

ያስተማራቸውን ሕብረተሰብ በቅንነትና በታማኝነት እያገለገሉ እንደሚገኙ በሆስፒታሉ ውስጥ የድንገተኛ ሕክምና ክፍል ባለሙያዋ ሲስተር ደግነሽ ሙኬና የወላድ እናቶች ክፍል ባለሙያ የሆኑት ታከለ ፋሪሰ ተናግረዋል።

የተገልጋዮችን እንግልት ለመቀነስ እና የተሻለ ህክምና አገልግሎት ለመስጠት በጋራ እየሰሩ መሆናችውን የጠቀሙት ባለሙያዎች ለሕክምና አገልገሎት አጋዥ የሆኑ አንዳንድ መሳሪያዎች ላይ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል።

ሆስፒታሉ በተለይ የተገልጋይ ማህበረሰብን ፍላጎት ለማርካት ተቋማዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ የተናገሩት ሀላሊ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሣሊኮ ሣሣ፥ በአንዳንድ የሥራ ክፍሎች ያሉ የሕክምና ማሳሪያዎች ላይ የተስተዋለው መጠነኛ ብልሽት በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ቢሆንም ተገልጋዮችን ለማረካት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለፃ፥ ከማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነት እና መድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜያት ከተገልጋዩ ሕብረተሰብ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውንና ለባለሙያዎች በትርፍ ሰዓት የሚከፈል ክፍያም በአግባቡ እየተከፈለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በወረዳው የጤና አጠባበቅ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ሕዝቅኤል ሜንታ በበኩላቸው፥ በጤና ተቋሙ ውስጥ የተበላሹና አገልግሎት የማይሰጡ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች መኖራቸውን በማረጋገጥ መሰል ግብዓቶችን በማሟላት የሕብረተሰቡን ዕርካታ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከወረዳና ዞን ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ችግሮችን በመለየት በየደረጃው ለመፍታት የተቀመጠ አቅጣጫ ስለመኖሩም ኃላፊው አስረድተዋል።

ዘጋቢ: ፍቃዱ ማቴዎስ – ከዋካ ጣቢያችን