ትምህርት ቤቶች በግቢያቸው የሚገኙ ትርፍ መሬቶችን በማልማት የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው ተጠቆመ
በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ የሻሸመኔ 1ኛ ደረጃና 2ኛ ሳይክል ትምህርት ቤት በግቢው የሚገኘውን ሰፊ የእርሻ መሬት የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ሰብሎችን በማልማት የውስጥ የገቢ አቅሙን ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ውድነህ ቦጋለ በሰጡት አስተያየት፤ የትምህርት ቤቱ መሬት ለም፣ የተከሉትን ሁሉ የሚያበቅል በመሆኑ ማንጎ፣ አፕል፣ ግሽጣ፣ ጎደሬ፣ ሙዝ፣ በቆሎና የመሳሰሉ ሰብሎችን በስፋት ማልማታቸውን ተናግረዋል።
አያይዘውም ትምህርት ቤቱን በውስጥ ገቢ ለማሳደግና ከተረጂነት ለማላቀቅ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በትምህርት ቤቱ ያሉ ክበባትንና አደረጃጀቶችን በመጠቀም በተግባር ወደ ሥራ መግባታቸውን የተናገሩት ርዕሰ መምህሩ፣ በምግብ እጥረት የተጎዱ ተማሪዎችንና ለአካባቢው የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንደሚያደርጉም አጫውተውናል።
ትምህርት ቤቱን ከጎበኙት መካከል አቶ ካሳሁን ደንቢና አበበ ከበደ በሰጡት አስተያየት፣ የትምህርት ቤቱ ይዞታ በቋሚና በጊዜያዊ ሰብሎች መሸፈኑ እንዳስደሰታቸው ገልፀው ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ይህን ተሞክሮ በመውሰድ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አካባቢው የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን፣ የሥራ ሥር ሰብሎችን የሚያበቅል ከመሆኑም ባሻገር ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ጋርም በተያያዘ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
በተለይም በአሁኑ ሰዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠፋና ምርቱም እየተመናመነ የሚገኘው የእንሰት ዝርያን ለመታደግና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
የቡና ማበብን ተከትሎና የተለያዩ ለማር ምርት ምቹ የሆኑ እፅዋቶች ያሉበት አካባቢ በመሆኑ በቀጣይ በዘመናዊ መንገድ ንብ የማነብ ልምድ በማሳደግም የትምህርት ቤቱን ሁለንተናዊ ገቢ በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደሚቻልም በመግለፅ።
የኮቾሬ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ መንገሻ፤ በወረዳው ካሉ ትምህርት ቤቶች መካከል የሻሸመኔ 1ኛ ደረጃና 2ኛ ሳይክል ትምህርት ቤት አንጋፋና ሞዴል መሆኑን ጠቁመው የእንሰት፣ የቡና፣ የሸንኮራ አገዳና አገር በቀል የፍራፍሬ ሰብሎችን በማምረት ከራሱ አልፎ ለገበያ በማቅረብ መንግሥት የጀመረውን የልማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የአካባቢው ሕብረተሰብ ከትምህርት ቤቱ መልካም ልምድ በመቅሰም በጓሮአቸው በአጭር ጊዜ በሚደርሱ የአትክልት ዝሪያዎችን በማልማት የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በሻሽመኔ ትምህርት ቤት ግቢ የለሙ ሰብሎችና ልዩ ልዩ ለፍራፍሬ የግቢውን ውበት ከመጠበቅ ባሻገር የአካባቢውንም ሥነ-ምህዳር ከማስተካከል አንጻር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን ግቢያቸውን ማልማት ይኖርባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ: እሥራኤል ብርሃኑ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
ትምህርት ቤቶች በግቢያቸው የሚገኙ ትርፍ መሬቶችን በማልማት የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው ተጠቆመ

More Stories
የግል ጤና ተቋማት ሙያዊ ስነምግባራቸውን ጠብቀው ተገቢ ግልጋሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቆመ
የጉራጊኛ ቋንቋ የስራ፣ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን በተላለፈው ውሳኔ መደሰታቸውን የእዣ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ
አሊያንስ ኮሌጅ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን በማፍራት የሀገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታወቀ