በዞኑ የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ መካሄድ መጀመሩ ተገለጸ

በዞኑ የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ መካሄድ መጀመሩ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጉራጌ ዞን የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ በዛሬው ዕለት በይፋ መጀመሩን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የተማሪዎች ምዝገባ በወቅቱ እንዲከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ መምሪያው ጥሪ አቅርቧል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በሰጡት መግለጫ በዞኑ የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ በዛሬው ዕለት በይፋ መጀመሩንና እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

ስለሆነም ምዝገባው እስከ ነሀሴ 30 ለማጠናቀቅ ከዞን ማዕከል እስከ ታችኛው መዋቅር ንቅናቄ በማካሄድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ተደርሷል ነው ያሉት።

በዞኑ በየአመቱ የተማሪዎች ምዝገባ በወቅቱ ባለመካሄዱና ትምህርት በወቅቱ ባለመጀመሩ ምክንያት የትምህርት ክፍለ ጊዜ በመባከኑ በተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ጠቁመው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ተማሪዎች በወቅቱ በመመዝገብ ትምህርት መጀመር እንደሚገባቸው አቶ መብራቴ ተናግረዋል።

በተለይም በዘንድሮ አመት በዞኑ በቅድመ አንደኛ ደረጃ 60 ሺህ 380፣ የጎልማሶች ትምህርት 45 ሺህ እና በመደበኛ 228 ሺህ 17 ተማሪዎች ምዝገባ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።

ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ወንዞችና ጅረቶች ሊሞሉ ስለሚችሉ አደጋ እንዳይከሰት ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው ትምህርት ቤት ቀርበው ማስመዝገብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በሁሉም በዞኑ ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች መስከረም 5/2018 ዓ/ም ትምህርት እንደሚጀመር ገልፀው የትምህርት አመራሩ ለመማር ማስተማር የሚያዘጋጁ ግብአቶችን የማሟላት፣ ግቢ የማስዋብ እንዲሁም ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።

በ2017 ዓ.ም ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምርት ገበታ እንዲመለሱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ኃላፊው ጠቁመዋል።

በዞኑ ምዝገባ በወቅቱ እንዲከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የመምሪያ ኃላፊው አቶ መብራቴ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወልደማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን