‎‎ወረዳው በስፋት እየለማ ያለውን የስንዴ ምርጥ ዘር ለክልሉ ዞኖች ማከፋፈል መጀመሩን አስታወቀ

‎‎ወረዳው በስፋት እየለማ ያለውን የስንዴ ምርጥ ዘር ለክልሉ ዞኖች ማከፋፈል መጀመሩን አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጌዴኦ ዞን የገደብ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት በወረዳውና አከባቢው በስፋት እየለማ ያለውን የስንዴ ምርጥ ዘር ለክልሉ ዞኖች ማከፋፈል መጀመሩን አስታውቋል።

‎ወረዳው በ2017/18 መኸር እርሻ ከ2 ሺህ 800 በላይ ሄክታር መሬት በዓመታዊ ሰብሎች ለመሸፈን አቅዶ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
‎‎
‎ወረዳው አምና በመኸር ወቅት በስፋት የስንዴ ምርት በማልማት በደቡብ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በኩል የጥራት ደረጃቸው የተረጋገጠ የስንዴ ምርጥ ዘር በጌዴኦ ልማት ማህበር አማካኝነት ለክልሉ ዞኖች እያቀረበ እንደሚገኝ የገደብ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡

የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ በተጨማሪ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ከመቀነስ አኳያ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ነው አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡

‎በዘንድሮ መኸር ከ2 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ፣ ቦቆሎ፣ ገብስ፣ ባቄላ እና ሌሎች ዓመታዊ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የጠቆሙት ኃላፊው፥ ለዚህም በቂ የአፈርና የግብዓት እንዲሁም በሰብል ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

‎የገደብ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ምትኩ በበኩላቸው በበልግ ወቅት ከለማው መሬት የደረሱ ሰብሎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውንና ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በተያዘው ኢኒሼቲቭ በሀይማኖት ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በቡና ኢንዱስትሪዎች የለማው የቦቆሎ ምርት በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‎በዘንድሮ የመኸር ወቅት አከባቢዎችን በኩታገጠም በማስተሳሰር በስንዴ፣ በገብስ፣ በባቄላ፣ በድንችና ሌሎች ሰብሎች የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው በመንግስት የተያዘውን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሻገር ራዕይን እውን ለማድረግ በትጋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‎በወረዳው የገደብ ጉበታ እና ባንቆ ጨልጨሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደር ታምራት ደያሶ እና ገበየሁ ጠቀቦ ከግብርና ልማት ሥራዎቻቸው ውጤት የተመጣጠነ ምግብ፣ ጤናማ የአኗኗር ሥርዓትና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆን መቻላቸውን ገልጸው የዘርፉ ባለሙያዎች እገዛ እጅጉን እየጠቀማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‎ለመኸር ወቅት መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ በሚገባ መዘጋጀታቸውን የጠቆሙት አርሶ አደሮቹ፥ አሁንም የተሻለ ምርት ለማግኘት አልመው ወደ ተግባር መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

‎ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን