ስፖርታዊ ውድድሮች ማህበረሰብን ከማቀራረብ ባሻገር ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ስለሚያስችሉ ሊጠናከሩ እንደሚገባ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል
በወልቂጤ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስፖርታዊ ውድድሮች ተጠናቀዋል።
በዚሁ ወቅት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የጤና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሙባሪክ ዘይኑ እንደገለጹት፤ ስፖርታዊ ውድድሮች ማህበረሰብን በማቀራረብ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲጎለብት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
መሰል ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞች የሚፈሩበት በመሆኑ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ሙባረክ ገልጸዋል።
በክረምት በጎ ፍቃድ ለመስራት የታቀዱ እቅዶችን ለመተግበር ቀሪ ጊዜያት ሰፊ የቅንጅት ስራዎች መስራት እንደሚየስፈልግም ጠቁመዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አስራት ታደለ በበኩላቸው፤ የክረምት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ ሲሆን የእግር ኳስና የፓራ ኦሎምፒክ ውድድሮች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የእግር ኳስ ውደድሩ ከዚህ ቀደም በከተማው ስፖርት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የቀድሞ የከተማው ወጣቶች ለማስታወስ የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል።
ውድድሩ ወጣቶች አልባሌ ቦታዎች እንዳይውሉ የሚያግዝ መሆኑን ያነሱት አቶ አስራት፤ በከተማው የሚገኙ ተተኪ ስፖርተኞችን ያበረታታል ብለዋል።
በውድድሩ ሲሳተፉ ካነጋገርናቸው ወጣቶች መካከል ወጣት አድናን ፋይሰልና ቢኒያም አብዮት ይገኙበታል። በክረምት ወቅት ጊዜያቸውን በስፖርት ልምምድ እያሳለፉ እንደነበር አስታውሰው ውድድሩ በመዘጋጀቱ ደስተኛ መሆናቸውን አስረድተዋል።
መሰል ውድድሮች መዘጋጀታቸው ልምምዳቸውን ለማጠናከር እንደሚረዳ ሲያነሱ በቀጣይም በሌሎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በስድስት ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የሰነበተው የፉትሳል የእግር ኳስ ውድድር በመዝገቡ ወልዴ ቤተሰብ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን በመርሃ ግብሩ በበጎ ፈቃደኞች የደም ልገሳ ተግባር ተከናውኗል።
ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በየጊዜው ህብረተሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባው ተገለፀ
ክሪስታል ፓላስ የኮሙዩኒቲ ሽልድ ዋንጫ ሻምፒዮን ሆነ
ኬሮድ የስፖርትና ልማት ማህበር ተተኪ አትሌቶች የሚፈሩበትና ለሀገራችን የአትሌቲክስ ዘርፍ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ የስፖርት ማህበር መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ