የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት “ኦገት” ለዘመናዊ የፍትህ ስርዓት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት “ኦገት” ለዘመናዊ የፍትህ ስርዓት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት “ኦገት” የማህበረሰቡን ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን በማጠናከር ለዘመናዊ የፍትህ ስርዓት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

“ኦገት” የዳኝነት ስርዓትን ጨምሮ የብሔረሰቡ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ሳይበረዙ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቀቤና ልዩ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

“ኦገት” ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት በቀቤና ብሔረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው ሲሆን በተለይም የኦገት ሽማግሌዎች በስነ-ምግባራቸው ሆነ በኑሮ ዘይቤ ለሌሎች አርዓያ መሆን የሚችሉና ከብሄረሰቡ ከማናቸውም ጎሳና ቤተሰብ በህዝቡ ሸንጎ ተገምግመው ይመረጣሉ፡፡

አዝማች መኪዩ ሀጅ ሁሴን እና ኢማም ሀያቱ ሻሚል የቀቤና ብሄረሰብ የኦገትና የሀገር ሽማግሌዎች ሲሆኑ በሰጡት አስተያየት የኦገት ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ዘመናዊ ህግ ካልነበረበት ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ብሔረሰቡ ሲተዳደርበትና ሲዳኝበት የመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኦገት የዳኝነት ስርዓት በብሔረሰቡ መካከልም ሆነ በሌሎች ወንድም ህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ከቀላል እስከ ከባድ የሚደርሱ ግጭቶች የሚዳኙበትና እርቅ የሚወርድበት ስርዓት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የብሄረሰቡ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ አንደሚገኝም ጠቁመዋል ፡፡

በተለይም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲጠፉና ጠቃሚ የሆኑ የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ በትኩረት እንደሚሰራም የኦገት ሽማግሌዎቹ ገልጸዋል ፡፡

በኦገት የዳኝነት ስርዓት መዋሸትና በሌሎች ላይ አድሎ መፈፀም የተወገዘ ተግባር ነው የሚሉት የኦገት ሽማግሌዎቹ ይህም ትክክለኛና ፍትሃዊ ውሳኔ ለማሳለፍ አስችሎታል ብለዋል፡፡

ኦገት የራሱ የሆነ መተዳደሪያ ደንብና ስርዓት እንዲሁም የስልጣን እርከን ያለው መሆኑን የገለፁት አስተያየት ሰጪዎቹ በኦገት የተቀመጡ አቅጣጫዎችና ድንጋጌዎችን ማፍረስ የተከለከለና ለቅጣት እንደሚዳርግም አስታወቀዋል ፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሙከረም ኑረዲን በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ በርካታ ግጭቶችና አለመግባባቶች በተለየ መልኩ በህግ የተከለከሉ ጉዳዮች ሲቀሩ ብሔረሰቡ የኦገት የዳኝነት ስርዓት እንዲሁም በየደረጃው በሚገኙ የሽምግልና የድርድር ስርዓቶች እልባት እያገኙ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም የብሔረሰቡ የኦገት ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ለዘመናዊ ፍትህ ስርዓት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

አቶ አብድልዋስ ሀጅ መሀመድአሚን የቀቤና ልዩ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሃላፊ ሲሆኑ በኦገት የሽምግልና ስርዓት ሰላም፣ አብሮት፣ መተሳሰብና ፍቅር ከመኖሩም ባሻገር ብሔረሰቡ እንደ ዛሬ ዘመናዊ የፍትህ ስርዓት ከመኖሩ አስቀድሞ ሲገለገልበት የቆየ ትልቅ እሴት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ኦገት” የብሔረሰቡ የአኗኗር፣የህይወት ልምድና ስርዓት መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር የማንነቱ መሰረት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባህላዊ የኦገት የዳኝነት ሥርዓትን ጨምሮ ሌሎችም የብሔረሰቡ እሴቶች ተጠብቀው ከትዉልድ ወደ ትዉልድ እንዲተላለፉ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን በማንሳት ካለው ሁለንተናዊ ፋይዳ አኳያ በቀጣይም ከሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ ስራ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ: ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን