ከ1 መቶ ሺህ በላይ መራጮች የ2017 የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምርጫ እንደሚሳተፉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ

ከ1 መቶ ሺህ በላይ መራጮች የ2017 የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምርጫ እንደሚሳተፉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ

ምርጫው ከነሃሴ 9 እስከ 11/2017 ዓ. ም እንደሚካሄድም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የ2017 ዓ. ም ምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጀማል አባመጫ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ከፌደራል ጀምሮ የሚደረገው የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መጅሊስ ማቋቋሚያ ምርጫ የረጂም ጊዜ የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ እንደነበር አቶ ጀማል በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በክልሉ ሁሉም ዞኖች ምርጫው ይካሄዳል ያሉት አቶ ጀማል ነገር ግን በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት ምርጫ የማይካሄድባቸው መስኪዶች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የድምጽ መስጫ ቀኑ ከነሃሴ 9 ጀምሮ እስከ ነሃሴ 11 ቀን 2017 ዓመተ ምህረት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

ምርጫው በአምስት ዘርፎች ማለትም በኡለማዎች፣ በምሁራን፣ በወጣቶች፣ በሴቶችና በሥራ ማህበራት ዘርፎች እንደሚካሄድ ነው አቶ ጀማል የገለጹት፡፡

በምርጫው 1 መቶ 5 ሺህ 1 መቶ 61 መራጮች በክልል ደረጃ መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡

ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ አካታችና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ በሁሉም መስኪዶች ውይይት መደረጉንም ነው የተናገሩት፡፡

ከክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጋርም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳንኤል መኩሪያ