የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የገቢ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፣ ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጌዴኦ ዞን ገቢዎች መምሪያ የ2017 የገቢ አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የጌዴኦ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌቱ ታምሩ እንዳብራሩት ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ዋነኛው አማራጭ መሆኑን ጠቁመው ገቢን ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ግብር ከፋይ የሕብረተሰብ ክፍሎች የበኩላቸወን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በዞኑ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አቶ ጌቱ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በ2018 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ በሁሉም መዋቅሮች ርብርብ እየተደረገበት እንደሚገኝም ኃላፊው አስገንዝበዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አሰተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዞኑ ሕብረተሰብ ዘንድ በርካታ የመሠረተ ልማት ፍላጎቶች በመኖራቸው መንግሥት የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረው ግብርን በታማኝነት በመክፈል ሁሉም ለሀገር ያለውን አጋርነት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበት አብራርተዋል።
የዞኑን የመልማት ፍላጎት እውን ለማድረግ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቶችን በማዘመን ልዩ ልዩ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የገቢ አቅም ለማሳደግ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በተለይም በመብራት ዝርጋታ፣ በንጹሕ የመጠጥ ዉሃ አቅርቦት፣ በመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታና የጤና ተቋማትን ለማስፋፋት በሕዝቡ ለረጅም ጊዜ ይጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሕዝብ የሚሰበሰበው ግብር ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል ብለዋልም።
ያለ ሕብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በሁሉም መስክ የተዋጣላት ሀገር መፍጠር አይቻልም፤ ሀገሪቷን ከድህነት ታሪክ ለማውጣትና ለማሻገር እያንዳንዱ ዜጋ በግብርና ታክስ አሰባሰብ ተግባራት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ያሉት የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ተመስገን ጥላሁን ናቸው።
በግብር ላይ የሚፈጸም የማጭበርበር ወንጀል የሀገርንና የሕዝብን ሕልውና የሚጎዳ በመሆኑ ይህን ድርጊት በሚፈጸሙ አካላት ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ መሥራት እንደሚገባ ተሳታፊዎች አስታውሰዋል።
ዘጋቢ :- እሥራኤል ብርሃኑ ከይርጋጨፌ ጣቢያችን።
More Stories
የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት “ኦገት” ለዘመናዊ የፍትህ ስርዓት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
ከ1 መቶ ሺህ በላይ መራጮች የ2017 የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምርጫ እንደሚሳተፉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል