የመጅሊስ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ የጉራጌ ዞን የመጅሊስ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ጽ/ቤት አሳሰበ

የመጅሊስ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ የጉራጌ ዞን የመጅሊስ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ጽ/ቤት አሳሰበ

ከነሐሴ 9 እስከ 11/2017 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ የጉራጌ ዞን የመጅሊስ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ጽ/ቤት አሳስቧል።

በዞኑ የመጅሊስ ምርጫን ለማካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል።

ጽህፈት ቤቱ በዞኑ በሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የጉራጌ ዞን የመጅሊስ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ጽ/ቤት ዋና ጸሃፊ አቶ ኑረዲን መሐመድ የመጅሊስ ምርጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከነገ ነሐሴ 9-11/2017 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ በመጥቀስ በጉራጌ ዞንም በሁሉም መዋቅሮች ምርጫውን ለማካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ያነሱት ዋና ጸሃፊው፤ ምርጫው ለሀገር ሰላም እና ለህዝቦች አንድነት መጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው ያስረዱት።

ምርጫው በአምስት ዘርፎች የሚከናወን ሲሆን ከነገ ነሐሴ 9-11/2017 ዓ.ም ድረስ የኡለማ፣ የምሁራን፣ የወጣቶች እና የሴቶች እንዲሁም የሰራተኛው ዘርፍ ምርጫዎች በቅደም ተከተላቸው መሠረት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

መራጮች ምርጫው ለሀገር ሰላምና ልማት መረጋገጥ ያለው ጠቀሜታ በመረዳት መታወቂያቸውንና ካርዳቸውን በመያዝ በየመስጅዱ በሚደረገው ምርጫ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በመገኘት ሀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው በማስገንዘብ ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸው ሀላፊነት እንዲወጡ ዋና ፀሃፊው አቶ ኑረዲን መሐመድ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን