በክልሉ የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ

በክልሉ የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለ20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በክልሉ የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

የዝግጅቱ አካል የሆነውና “ኪነ ጥበብ ለክልላችን ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተግባር ሥልጠና በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መሰጠት ተጀምሯል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ፣ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቋንቋ፣ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው በተቋቋመበት አቅራቢያ የሚገኙ ፍላጎቶችን መነሻ በማድረግ በርካታ ሥራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ የሥልጠናውን መርሐግብር ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት ክልሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ለባህል ልማት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

በ20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ዕለት በክልሉ የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ ልዩ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ የገለጹት አቶ ሳሙኤል በዚህም አዳዲስ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይቀርባሉ ብለዋል።

በሥልጠናው የተሳተፉ ተወካዮችም ሥልጠናውን በአግባቡ እንዲከታተሉና ወደ ታች ሲወርዱም ሌሎችን የማሰልጠን ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ገመቹ አረቦ በበኩላቸው የ20ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በብቃት ሰርተን ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች የጣሉብንን ኃላፊነት በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

በእስካሁኑ ሂደት ከወሰድነው ተሞክሮ በመነሳት በተሻለ ዝግጅት ባህላችንን ለሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ገመቹ ለዚህም ሰልጣኞች ሥልጠናውን በአግባቡ እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

ዳንኤል ግዛቸው ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስፋው ዳንኤል ደግሞ ከሀዲያ ዞን ባህል ኪነት ቡድን የውዝዋዜ አሰልጣኞች ሲሆኑ፥ በሰጡት አስተያየትም ሥልጠናው እርስ በርሳቸው ለመተዋወቅና ተሞክሮ ለመቅሰም እንዲሁም በብሔር ብሔረሰቦች ቀን የተሻለ ዝግጅት ለማቅረብ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

በሥልጠናው በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የኪነት ቡድን አባላት እየተሳተፉ ሲሆን ሥልጠናውም ከነሀሴ 7 እስከ ጳጉሜን 2/2017 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ወር ያህል የሚሰጥ ይሆናል።

ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን