በ2018 ከ502 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2018 ዓ.ም የታቀዱ ተግባራት መፈፀም የሚያስችሉ የካፒታል እና አስተዳደራዊ ወጪዎችን ለመሸፈን 502 ሚሊዮን 958 ሺህ 599 ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በከተማ አስተዳደሩ የ2017 ዓ.ም የገቢ አፈፃፀምና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።
የሳውላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ኩማ በ2017 ዓ.ም የከተማዉን የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት መፈፀም እንዲቻል እንዲሁም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ፋይናንስ ለማድረግ በአጠቃላይ 317 ሚሊዮን 707 ሺህ 619 ብር ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ የተሠራ እንደነበር አስታውሰው 244 ሚሊዮን 199 ሺህ 053 ብር መስብስብ መቻሉን ገልጸዋል።
ከ2016 ዓ.ም አፈፃፀም ጋር ስናነፃጽረዉ 75 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታሁን በ2018 በበጀት ዓመት የታቀዱ ሥራዎችን መፈፀም የሚያስችል የካፒታል እና አስተዳደራዊ ወጪዎችን የሚሸፍን ፋይናንሻል የገቢ ዕቅድ 502 ሚሊዮን 958 ሺህ 599 ብር ሲሆን ይህም ካለፈዉ በጀት ዓመት ዕቅድ ጋር ስነፃፀር 80 በመቶ ብልጫ አለዉ ብለዋል።
የሳውላ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ንጉሤ መኮንን የገቢ ሥራዎች በጥንቃቄ በመመራታቸው በከተማው የቆሙ ካፒታል ሥራዎችን ማስቀጠል የተቻለ ከመሆኑ ባሻገር ልዩ ልዩ ማሽነሪዎች ግዢ ጭምር መከናወኑን ተናግረዋል።
የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ኩማ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሳዩት የተቋሙ የሰው ሀይል ምርታማነት መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልጸው፥ የአከራይ ተከራይ፣ የVAT እና TOT ግብር አሰባሰብ በደካማ ጎን የተገመገሙ ጉዳዮች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ኃላፊው ግብርን በቴሌ ብር ብቻ ለማስከፈል በተደረገው ጥረት 88 በመቶ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል።
ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት የገቢ ሥረዐቱን ማዘመን፣ ከደረሰኝ አቆራረጥ ጋር የተያያዙ ውስንነቶችንና ህገ ወጥነቶችን ለይቶ ለህግ ማቅረብና ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ማስቻል ይገባል ብለዋል።
የማዘጋጃ ቤት ገቢ አሰባሰብ ያሳዬው እድገት ይበል የሚያሠኝ መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ በህግ የተያዙ የገቢ ማጭበርበር ክሶችአፋጣኝ እልባት እንደሚሹ አንስተው ህገ ወጥነት የሚታይባቸው የተቋማት የግዢ ሥርዓቶች መታረም ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢ/ር ዳግማዊ አየለ የግብር ከፋዮች የደረጃ ሽግግር ረገድ በነጋዴው ዘንድ የሚስተዋሉ ስጋቶችን ለመቅረፍ ሰፊ የግዛቤ ሥራ እንደሚያስፈልገው ገልጸው፥ ጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ጥቅም ላይ ለማዋልና የከተማውን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ የገቢ ባለሙያው ለንግዱ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ዙሪያ የታየው ውስንነትና የአከራይ ተከራይ ልየታ አድርጎ ተገቢውን ግበር ከመሠብሰብ ረገድ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሣውላ ካምፓስ መምህር ኤፍታህ ህዝቅኤል አማካይነት ከ2012 እስከ 2016 ዓ.ም በየገቢ ርዕሱ ሊሰበሰብ የሚገባ የንግድ ገቢ ግብርን አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት በከተማዋ በተገቢው መንገድ ግብር መሰብሰብ ባለመቻሉ በርካታ ሀብት ማጣቷን አብራርተዋል።
በመጨረሻም በዘንድሮው የግብር አከፋፈል ከፍተኛ ደረጃን ለያዙ የየደረጃው ነጋዴዎች የዋንጫና ሠርተፍኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ
የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
በከተማው እየታየ ያለው የልማት መነቃቃት ቀጣይነት እንዲኖረው የጀመርነውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የገደብ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ