የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የኣሪ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የኣሪ ሕዝብ ልማት ማህበር በጂንካ ከተማ ኩሬ ቀበሌ አከባቢ በ15 ሄክታር መሬት ላይ መልካሳ ሁለት የተሰኘ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት እያከናወነ መሆኑ አስታውቋል።

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የኣሪ ሕዝብ ልማት ማህበር ምክትል የቦርድ ሰቢሳቢ አቶ አብርሃም አታ እንደገለፁት ልማት ማህበሩ በግብርናው ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን በጤና፣ በትምህርት፣ በምርምርና ፈጠራ ሥራዎች፣ በማህበራዊ አገልግሎቶች የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት የተቋቋመ ሀገር በቀል ማህበር መሆኑን አስረድተዋል።

በዞኑ የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ሰብሎችን ከማህበራትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የብዜት ሥራውን በልዩ ትኩረት እንደሚመሩ አቶ አብርሃም ተናግረዋል፡፡

የኣሪ ሕዝብ ልማት ማህበር ለኢንቨስትመንት ከተረከበው 300 ሄክታር መሬት 15 ሄክታር መሬት በመኸሩ እርሻ በሙሉ ፖኬጅ በበቆሎ ምርጥ ዘር ለመሸፈን ያደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ፥ ለውጤታማነቱ መምሪያው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ በበኩላቸው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ልማት ማህበሩ በከተማ ግብርና ዘርፍ ለሚያከናውናቸው ተግባር የከተማ አስተዳደሩ ሁለንተናዊ ድጋፍና እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ልማት ማህበሩ በ2011 ዓ.ም ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ከተቋቋመ በስድስት አመት ቢሆነውም በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን የገለፁት የልማት ማህበሩ ሥራአስኪያጅ አቶ ዳንኤል ወይካ፥ ከ25 ዓመት በላይ በባለሀብት እጅ ሳይለማ የቆየውን የኢንቨስትመንት መሬት ተረክቦ መልካሳ ሁለት የተሰኘ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት መጀመሩን አስረድተዋል።

ልማት ማህበሩ በአከባቢያቸው የሚያደርገው የልማት እንቅስቃሴ የሥራ ዕድል እንደፈጠረላቸው የአከባቢው ነዋሪዎችና ወጣቶች ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን