‎በከተማው እየታየ ያለው የልማት መነቃቃት ቀጣይነት እንዲኖረው የጀመርነውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የገደብ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

‎በከተማው እየታየ ያለው የልማት መነቃቃት ቀጣይነት እንዲኖረው የጀመርነውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የገደብ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

‎ሀዋሳ፣ ነሐሴ 07/2017 ኣ.ም (ደሬቴድ) በከተማው እየታየ ያለው የልማት መነቃቃት ቀጣይነት እንዲኖረው የጀመርነውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በጌዴኦ ዞን የገደብ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

‎የከተማው አስተዳደር በበኩሉ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ለኢንቨስትመንት ሳቢ የማድረጉ ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

‎ካነጋገርናቸው የገደብ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አብድዩ በራሶ ፣ መለሰ ዋቆ እና ሌሎችም ከተማዋ ካላት ዕድሜ አንጻር በተገቢው መንገድ ሳታድግ መቆየቷን አስታውሰው ‎ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በከተማዋ እየታዩ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎች የነዋሪዎቿን የዘመናት ጥያቄዎች እየመለሱ እንደሆነ ያነሱት ነዋሪዎቹ አመራሩ ከህዝብ ጋር የፈጠረው ጠንካራ አንድነት እየተመዘገቡ ላሉ ለውጦች በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

‎በከተማው የኮሪደር ልማት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቤታቸውንና ሱቃቸውን ከማፍረስ ጀምሮ ለልማቱ ያላቸውን አጋርነት እያሳዩ መሆናቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ በከተማዋ እየታየ ያለው የልማት መነቃቃት ቀጣይነት እንዲኖረው ድጋፋቸውን አጠናክሮ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

‎የገደብ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ ከተማ በተጠናቀቀው 2017 የበጀት ዓመት ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ፕላን ከማስከበር አንስቶ በዕቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

‎ንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ፣ የድልድይ ግንባታ እና ሌሎች የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የከተማዋን ነዋሪዎችን ባሳተፈ መልኩ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡

‎የገደብ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታሪኩ ሮቤ በበኩላቸው ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው ከተማዋ ያላትን ምቹ ዕድሎች ተጠቅመው በሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በከተማ ግብርና ዘርፎች ላይ ለመሰማራት በርካቶች ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

‎ከተማ አስተዳደሩም በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ቦታ ከማዘጋጀት አንስቶ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

‎ዘጋቢ:- ሳሙኤል በቀለ ከይርጋጨፌ ጣቢያችን