“መንገድ ላይ እያረፍኩ ነበር ትምህርት ቤት የምሄደው” – ወ/ሮ ፍሬህይወት አይሴ
በአስፋው አማረ
ጀግንነት በተለያዩ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል፡፡ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ማለፍና ከሁኔታው በላይ መሆን ከጀግንነት ጎራ ይመደባል፡፡ አይቻልም የሚለውን ሀሳብ ሰብሮ በመውጣት ለስኬት መብቃት በራሱ ጀግንነት ነው፡፡
በዛሬው ችያለሁ አምዳችን ይዘንላችሁ የቀረብነው እንስት አካል ጉዳተኝነት ሳይበግራቸው ከገጠር ወደ ከተማ በመውጣት ራሳቸውን ለመቀየር ጥረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ወ/ሮ ፍሬህይወት አይሴ ይባላሉ። የተወለዱት በከምባታ ዞን ዶዮገና ወረዳ በዶገና ቀበሌ ነው፡፡ በልጅነታቸው በደረሰባቸው የአካል ጉዳት ምክንያት እንደ አካባቢው ልጆች እንደፈለጉ መጫወት አይችሉም ነበር፡፡
የደረሰባቸውን አካል ጉዳት ሁኔታውን ሲያስታውሱን፦
“የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ አባቴ ወደ እርሻ፣ እናቴ ደግሞ ወደ ገበያ ሲሄዱ እኔን ጎረቤት አስቀምጠውኝ ነበር የሄዱት፡፡ በወቅቱ እኔን ተሸክማ የነበረችው የጎረቤት ልጅ ከእጇ እወድቅና ቀኝ እግሬ ላይ ጉዳት ይደርሳል፡፡
“በወቅቱ የሁለት ዓመት ልጅ ስለነበርኩኝ መናገር አልችልም ነበር። ሁኔታውን እነሱ ባለመረዳታቸው በጊዜ ወደ ህክምና አልወሰዱኝም፡፡ በጊዜ ሂደት ቀኝ እግሬ ላይ ጉዳት መድረሱን ነበር ያወቁት።” ሲሉ አጫውተውናል፡፡
በወቅቱ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በዶገና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ከ1ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በዚህ ሁሉ አካል ገዳተኝነታቸው ምንም ሳይመስላቸው እና ካሰቡበት ለመድረስ ትምህርታቸውን አጥብቀው መያዝ ነበረባቸው፡፡
በዚህ ምክንያት ከትውልድ ቀያቸው የተሻለ ትምህርት ፍለጋ ጥቁር ውሃ (ቢሻን ጉራቻ) ከተማ አጎታቸው ጋር በመጠጋት ከ5ኛ ክፍል አንድ ደረጃ በመቀነስ የ4ኛ ክፍል ትምህርታቸውንና ከ4ኛ እስከ 7ኛ ክፍል ተከታትለዋል፡፡
በመቀጠል 8ኛ እና 9ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በዳቶ ተከታትለዋል። ከጥቁር ውሃ እስከ ዳቶ እየተመላለሱ ነበር የሚማሩት፡፡ ሲራመዱ ደግሞ ቀኝ እጃቸውን ቀኝ እግራቸው ላይ በማስደገፍ ነበር የሚራመዱት፡፡ ይህን ተከትሎ ከጥዋቱ 12 ሰዓት ላይ ተነስተው ዳቶ 2 ሰዓት ነበር የሚደርሱት፡፡
በዚህም ምክንያት መንገድ ላይ በጣም ስለሚደክማቸው እያረፉ ነበር እየተመላለሱ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ደግሞ ትምህርታቸውን በጣም ስለሚወዱ ነበር፡፡ የደረጃ ተማሪ እንደነበሩም ወ/ሮ ፍሬህይወት አጫውተናል፡፡
“ትምህርቴን ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ መቀጠል አልቻልኩም፡፡ በጣም ከምወደው ከትምህርት ለመለያየት (ለማቆም) ተገደድኩ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ የአጎቴ ቤተሰብ እኔን ለማገዝና ለማስተማር ፈቃደኛ አልነበሩም” ሲሉ ትምህርታቸውን ለማቆም የተገደዱበትን አጋጣሚ ተናግረዋል፡፡
“ይህ ሁኔታ ቢገጥምም ከአካል ጉዳተኝነቴ ጋር ማያያዝ አልፈለኩም። መማር ካልቻልኩ መነገድ እችላለሁ የሚል ሀሳብ ውስጤ ይመላለስ ጀመረ፡፡” ሲሉ ወደ ንግድ ዓለም ለመግባት አስበው እንደነበር አውግተውናል፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር ወደ ንግድ ዓለም ለመግባት የተገደዱት፡፡ በወቅቱ ለእሳቸው ሥራ አመቺ የሆነው ደግሞ ቡና እና ፍራፍሬ ንግድ ነበር፡፡ ይህንንም ሥራ ከሐዋሳ ወደ ጥቁር ውሃ ከተማ ሲገባ በስተግራ በኩል ከማሪያም ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ሸራ ወጥረው ነበር የሚሠሩት፡፡
ሥራውም በጊዜ ሂደት በጣም ጥሩ እየሆነላቸው መጣ፡፡ በርካታ ደንበኞችንም ማፍራት መቻላቸውንም አስታውሰውናል። እቁብ በመግባት ገንዘብ ማጠራቀም ቻሉ። ከዚህ በኋላ ነበር ወደ ሌላ ሥራ ለመግባት ማሰብ የጀመሩት፡፡
“ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በመሆን ከጥቁር ውሃ ወደ ሐዋሳ ዜሮ አምስት ሰፈር ገባሁ። ከዚያም ቤት ተከራይቼ የማገዶ እንጨት፣ ቡና እና ከሰል መነገድ ጀመርኩ፡፡ ሥራው በጣም ጥሩ ሆነና ደንበኞችን አፈራሁ፡፡ ትዳር መስርቼም ሁለት ልጆችን ማፍራት ቻልኩ፡፡” በማለትም አጫውተውናል፡፡
እሳቸው መማር እየፈለጉ ያልቻሉትን ትምህርት ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ከሁለተኛ ወደ ሶስተኛ ክፍል የተዛወረች ስትሆን ሁለተኛዋ ደግሞ ከቅድመ መደበኛ ወደ አንደኛ ክፍል ተዛውራለች፡፡
“ሥራውን በማስፋፋት ደረቅ እንጀራ ማከፋፈል ጀመርኩ፡፡ እንጀራው ተወዳጅ እየሆነ ሲመጣም በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ቻልኩ፡፡ የመጀመሪያ ልጄን በወለድኩ ጊዜ ሥራውን ባለቤቴ ወጣ ገባ እያለ ይሠራ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አከራዮቼ ሱቁን ልቀቂ እኛ እንሰራበታለን የሚል መጥፎ ዜና አበሰሩኝ” ሲሉ ሥራቸው መስተጓጉሉን ይናገራሉ፡፡
“ምናልባት የቤት ኪራዩ ብሩ አንሷቸው ነው ብዬ በማሰብ ብር ልጨምርላችሁ ብላቸው አይሆንም የሚል መልስ ነበር የሰጡኝ። በዚህ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ የሱቅ ሥራዬን ለመዝጋት ተገደድኩኝ” በማለት ይናገራሉ፡፡
ከዚህ በኋላ የሱቅ ሥራውን ትተው የቤት እመቤት ለመሆን መገደዳቸውን ይናገራሉ። ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ተስፋ የማይቆርጡት ወ/ሮ ፍሬህይወት ሥራ መስራት እፈልጋለሁ ብለው ሲናገሩ የሰሙት እህታቸውና ባለቤታቸው “ምን ዓይነት ሥራ ነው የሚሰሩት” በማለት ቀልደውባቸዋል፡፡
በአጋጣሚ አንድ ወቅት ሱቅ በሚሰሩበት ጊዜ የተዋወቁት ርብቃ አማረ የምትባል ልጅ ነበረች፡፡ “ሥራ መስራት እፈልጋለሁ” ብለውም ለርብቃ ነገሯት። ርብቃም በእሳቸው ሀሳብ ተስማምታ ሥራ ፈልጋ በተመላላሽ ሰራተኛነት መቀጠር ችለዋል፡፡
“በተለይም ሥራ የምታሰራኝ ወጣት የሰው ችግር የምትረዳ ናት፡፡ ዘመኗን እግዚአብሔር ይባርክ፡፡ በጣም መልካም ሴት ናት፡፡ አካል ጉዳተኛነቴን ምንም ሳታይ ትችያለሽ ብላ አምና ቀጥራኝ ሥራ እሷ ጋር ከጀመርኩ አራተኛ ዓመቴን አስቆጥሬያለሁ። ትልቅ አክብሮትና አድናቆት አለኝ” በማለት ስለወጣቷ አሰሪዋ አውርተው አይጠግቡም።
ሥራ የሚወዱት ወ/ሮ ፍሬህይወት ከተመላላሽ ሥራቸው በተጨማሪ ቅቤ ከትውልድ አካባቢያቸው በማምጣት ለተጠቃሚ በማዞር እየሸጡ እንደሚተዳደሩ ይናገራሉ፡፡
“አንድ ሰው ጠንክሮ ከሰራ መለወጥና መቀየር ይችላል፡፡ በአንድ ምሽት የሚፈጠር ለውጥ የለም፡፡ ጠንክረን በተሰማራንበት ሙያ ከሰራን መቀየርና መለወጥ እንችላለን።” የሚለውን ምክረ ሀሳባቸውን ይሰነዝራሉ።
More Stories
“በእጅ ጋሪ ያመላልሱኝ ነበር” – ተወዳ መንጌ
የስም ነገር
“እግር ኳስ ቢያሳምመኝም ቂም አልያዝኩበትም”