የትምህርት ብክነትና የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥን ለማስቀረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ አሳሰቡ
የዞኑ ትምህርት መምርያ የ2017 ዓ.ም የክረምት ስራ አፈፃፀም እና የ2018 ዓ.ም የመደበኛና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቅበላ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዚህ ወቅት እንዳሉት ትምህርት የሁሉም ነገር መሰረት ነው በመሆኑም የትምህርት ብክነትና የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥን ለማስቀረት በትኩረት መስራት ያሻል።
የትምህርት ልማት ስራዎችን ለማሻሻልና ተግባራዊ ለማድረግ ካለፉት ሦስት አመታት ጀምሮ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱን አቶ ላጫ አስታውሰው በተለይም የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሻሻል፣ የመማሪያ ግብአቶች የማሟላትና መምህራንን የማብቃት ተግባር ላይ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ተማሪዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ተገኝተው እንዲመዘገቡ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ውጤት በተመለከተ ከአለፉት አመታት ሲነፃፀር መሻሻሎች መኖሩን ጠቁመው በቀጣይም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ትውልዱ ለትምህርት ያለውን ተሳትፎ የማሳደግ ተግባር ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በተለይም በአመቱ መጀመርያ የክፍለ ጊዜ ብክነት እንዳያጋጥም የተማሪዎች የቅበላ ሂደት እስከ ታችኛው መዋቅር በመወረድ የመቀስቀስ ስራ መስራት እንደሚገባም አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ዜጎች ወደ ትምህርት ቤት የማስገባት እና የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስ ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል ሲሉም ገልፀዋል።
የ2018 ትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሃሴ 12 እስከ ጳጉሜ 5 በመሆኑ ለተፈፃሚነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካል በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ መብራቴ አመላክተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት ተማሪዎች በቀጣይ ለመደበኛው ክፍል ጊዜ በሚያዘጋጃቸው ተግባር ላይ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው በተለይም ትምህርት ቤቶች የማደስና የማስዋብ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን አንስተዋል።
አያይዘውም በመማር ማስተማር ተግባር ላይ የትምህርት ብክነት እንዳይፈጠር የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ቅበላ በተመለከተ በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ እርካብነሽ ወልደማርቆስ
More Stories
በክልሉ የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ
በ2018 ከ502 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ