የምዕራብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2018 በጀት ከ1.9 ቢልዮን ብር በላይ አጸደቀ

የምዕራብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2018 በጀት ከ1.9 ቢልዮን ብር በላይ አጸደቀ

ምክር ቤቱ በዞኑ ባሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ውይይት አደርጎ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
‎የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ኬኒ የ2017ዓም ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2018 ጠቋሚ ዕቅድ ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡበት ወቅት፡- በበጀት ዓመቱ በዋና ዋና እና በሆርቲካልቸር ሰብሎች 211ሺ ሄ/ር በክላስተር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸው በዚህም በመኸርና በበልግ 5.4 ሚልዬን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
‎‎
‎በዞኑ 50 የቡና አልሚ ባለሀብቶች እና አቅራቢ ነጋዴዎች መኖራቸውን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 596 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልፀዋል ።
‎ከትምህርት ውጤታማነትና ጥራት ጋር ተያይዞ በዞኑ በበጀት ዓመቱ ያጋጠመው ስብራት ላይ በጋራ በመረባረብ የተሰራ ሲሆን በ2018 በቂ ዝግጅት በማድግ እና ልዩ ትኩረት በመስጠት ለትምህርት እድሜያቸው የደረሱትን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲገቡ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ይሰራል ብለዋል ።

‎የወባ በሽታን መከላከል እና ቁጥጥር ላይ ከፍተኛ ጫና ባለባቸው ወረዳዎች የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር በቤት ውስጥ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት እና አጎበር ስርጭት እንዲሁም የወባ መራቢያ ስፍራዎችን በማዳፈንና በማፍሰስ የስርጭት ምጣኔውን ለመቀነስ አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቃል ብለዋል ።

አብሮነትና አንድነትን በማጠናከር የሰላም እሴቶችን መስበክ፣ ዘላቂነት ያለው ሰላም መገንባት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው ያሉት አስተዳዳሪው በበጀት አመቱ የዞኑን ሰላም ለማስጠበቅ ከፌደራል ከክልል መንግስታት ጋር በጋራ በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው ከ700 በላይ ሚሊሻ በማሰልጠን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።
ተጀምረው ያልተጠናቀቁና በየግዜው የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆኑ የመጡ የሶላር መብራት ዝርጋታ ዞኑ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

‎በየጊዜው የህዝቡ እሮሮ እየሆነ የመጣው የዋጋ ንረትና የመሰረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ወጋ መናር፣ የትራንስፖርት እጥረት፣ የታሪፍ ጭማሪ፣ የነዳጅ ማደያዎች በአግባቡ አለማሰራጨት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

‎‎
በመጨረሻም ለዞኑ 2018 በጀት አመት እቅድ ማስፈጸሚያ እንዲሆን 1ቢሊዬን 958ሚሊዬን 797ሺ 203 ብር በጀት ያጸደቀ ሲሆን የተለያዩ ሹመቶችን በመስጠት ጉባኤው ተጠናቅቋል፡፡

‎ዘጋቢ፡ ዮናስ ወ/ገብርኤል ከሚዛን ጣቢያችን