የተፈጥሮ መስህቦችን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሸካ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበው የሸካ ጥብቅ ደን ውስጥ 41 ፏፏቴዎች፣ 17 ዋሻዎችና 52 የማዕድን ውሃ (ሆራ) እንደሚገኙ የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።
በዞኑ ያሉትን የቱሪስት መዳራሻዎችን ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ ወደ ሀብት የመቀየሩ ስራ በ2018 በጀት ዓመት ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ተናግረዋል።
በዓለም የትምህርት ሳይንስና ባህል ተቋም”UNESCO” ሀብትነት ከተመዘገበው የሸካ ጥብቅ ደን ውስጥ መስህቦች በቱሪስት መዳረሻነት መለየታቸውን አስተዳዳሪው ይፋ አድርገዋል።
በዞኑ አራት የደጋ ሐይቆች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን ከእነሱም መካከል ከባህር ጠለል በላይ 2ሺህ 7መቶ ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የጋንዶዎቺ ሐይቅ ዋነኛውና ትልቁ ሲሆን፣ ሙርሌ ቁጥር 1እና ቁጥር 2 ፣ እንዲሁም ሾሺ ተጠቃሾች ናቸው።
የጋንዶዎቺ ሐይቅን ለጎበኚዎች ምቹ ለማድረግ በበጀት ዓመቱ በዞኑ የጋራ ዕቅድ 3 ነጥብ 1 ኪሎሜትር ከ 6 ሚለየን ብር በላይ በሆነ ወጪ መሰራቱን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ከመንገዱ ጫፍ እስከ ሐይቁ መዳረሻ በማሽን የማይቆፈረውን ቦታ በመሃንዲሶች ምክረ-ሃሳብ መወጣጫ መንገዶችን በመስራት የተለያዩ ባለሀብቶችን በመሳብ ሎጆችን የመስራት ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በእነዚህ ሀብቶች ላይ በትኩረት ለመስራት በዞኑ ያሉት ወረዳዎች ማህበረሰቡን በማስተባበር የመንገድ መዳረሻዎችን እንዲሰሩ የአሰራር ስርዓት ይዘረጋል ብለዋል።
የአካባቢው ወጣቶችና የማህበረሰብ አንቂዎች የጀመሩትን የሀገር ሀብት የማስተዋወቅ ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉና ያለውን ሀብት የማወቅና የማስተዋወቅ ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና አስተዳዳሪ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ ካሳሁን ደንበሎ – ከማሻ ጣቢያችን
የተፈጥሮ መስህቦችን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሸካ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

More Stories
የህፃናትን ጤናማነት ለመጠበቅ ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በኮሬ ዞን የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መልሶ የማደራጀት ምክክር መድረክ ተካሄደ