የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱ ያለው ፋይዳ የጎላ ነው ሲሉ አንዳንድ የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ተማሪዎች ተናገሩ
የከተማው ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት በበኩሉ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የትምህርት ስብራት መጠገንና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል አቅዶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
ተማሪ ቨሮኒካ መኩሪያ፣ ሶፎኒያ ሳሙኤልና ሌሎችም በከተማው የደብረ ምህረት ቅድስት ኪዳነምህረትና ፍቅር ፍሬ ርሆቦት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የክረምት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ያገኘናቸው ተማሪዎች ሲሆኑ ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅደው እየተማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ አክለውም የተሻለ ወጤት ለማስመዝገብ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ያለው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ ሌሎች ተማሪዎችም የእረፍት ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ከማሳልፍ አሁን ላይ እየተሰጠ ያለውን ትምህርት በመከታተል ለቀጣይ ትምህርታቸው እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።
መምህር ሲሳይ በየነ እና መምህር ፍሬሰላም አዳነ በትምህርት ቤቶቹ የክረምት ትምህርት ሲያስተባብሩ ያገኘናቸው ሲሆኑ፤ ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ ዕውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግና የትምህርት ስብራት ለመጠገን የሁላችንንም ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ በእረፍት ጊዜያችን በማጠናከሪያ እምህርትና መሰረታዊ የኮምፒውተር ክህሎት ስልጠና በመስጠት ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ምስጋናው በለጠና አቶ ታረቀኝ ረታ የይርጋጨፌ ቅድስት ኪዳነምህረት እና ሮሆቦት መካከለኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ናቸው።
በ2016 ዓ.ም የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለወጣቶች በመሰጠቱ እንደ ትምህርት ቤታቸው የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት 94 በመቶ ከነበረበት ዘንድሮ በሁለቱም የክፍል ደረጃዎች መቶ በመቶ የማለፊያ ውጤት መመዝገቡን መነሻ በማድረግ በ2017 ዓ.ም በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ሆርዶፋ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር የገጠመንን የትምህርት ስብራት ለመጠገንና በስነ-ምግባር የታነፀ ብቁ ዜጋን ለማፍራት የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ተማሪዎች በዕረፍት ጊዜያቸው አልባሌ ቦታ ከመዋል ተቆጥበው ለቀጣይ አመት እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል።
አክለውም በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የትምህርት ስብራት ለመጠገንና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዘጋቢ: ጽጌ ደምሴ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት “ኦገት” ለዘመናዊ የፍትህ ስርዓት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
ከ1 መቶ ሺህ በላይ መራጮች የ2017 የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምርጫ እንደሚሳተፉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ
የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የገቢ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ