የኮሪደር ልማት ስራዎች ለከተማ ዕድገት ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ

የኮሪደር ልማት ስራዎች ለከተማ ዕድገት ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአርባምንጭ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ለከተማው ዕድገት ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኮሪደር ልማት ስራን ጨምሮ በከተማው እየተከናወኑ ላሉ መሠረተ ልማቶች ህብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጠይቋል።

በሀገሪቱ በርካታ ከተሞች ላይ የኮሪደር ልማት ስራዎች መጀመራቸው ለከተሞች ዕድገትና ውበት ያላቸው አበርክቶ የላቀ መሆኑ ይነገራል።

በአርባ ምንጭ ከተማ የኩልፎ ወንዝ ዳርቻን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች አበረታች መሆናቸውም ተመልክቷል ።

የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅና የመሠረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስለሺ ደነቀ፥ በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፥ በኩልፎ ወንዝ ዳርቻ እየተሰራ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረጉም በዘለለ ለወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች አቶ ታገለኝ ተስፋዬ፣ መምህር ሀይሉ፣ አለማዬሁ እና ወ/ሮ ቤተልሔም ናኦስ እንደተናገሩት በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የመንገድ ዳር ልማት ስራዎች ለከተማው ዕድገት መነቃቃትን ከመፍጠሩም ባሻገር ለነዋሪዎቿም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።

የመንገድ ዳር ልማት ስራዎችን ጨምሮ በከተማው እየተከናወኑ ላሉ የተለያዩ መሠረተ ልማት ስራዎች የበኩላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል ።

አንዳንድ በሥራው እየተሳተፉ ያገኘናቸው ወጣቶችም የመንገድ ዳር ልማት ስራዎች በመጀመራቸው የስራ ዕድል በመፈጠሩ መደሰታቸውን ገልፀዋል ።

ዘጋቢ: እንጃ ገልሲሞ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን