በጎፋ ዞን በ2018 በጀት ዓመት ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ

በጎፋ ዞን በ2018 በጀት ዓመት ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ

የዞኑ ገቢዎች መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ ባዘጋጀው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፤ በገቢ አሰባሰብ ሂደት ላይ የሚስተዋሉ የግብር ስወራና ሌሎች ክፍተቶችን በዘላቂነት በመፍታት እና ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር ረገድ በየደረጃው የሚገኙ የገቢ እና ባለድርሻ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል የተጣለባቸውን የዜግነት ግዴታ በተገቢው ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የገቢ አቅማችንን በማሳደግ ያሉንን ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም የህዝቡን አዳጊ የልማት ፍላጎት ለመመለስ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ላይ አማራጮችን በማስፋት ዕቅዱን ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ወልደሚካኤል መኮንን በበኩላቸው፤ በ2017 በጀት ዓመት ከመደበኛ እና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አብራርተዋል።

በ2018 የበጀት ዓመት ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም ገልጸዋል።

ውዝፍ ግብር አሟጦ አለመሰብሰብ ሚዛናዊ ያልሆነ ግብር ግመታ፣ በጥረት መሰብሰብ ላይ ትኩረት አለመስጠት፣ የገጠር መሬት ገቢን አሟጦ አለመሰብሰብ፣ ታክስ ስወራና ማጭበርበር መበራከት በ2017 የበጀት ዓመት የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የግብር አሰባሰብ ሥርዓትን በማዘመን የህዝቡን የመልማት ፍላጎት ለማርካትና የመንግስትን የወጪ ፍላጎትን ለመሸፈን ከወትሮው በተለየ ትኩረት ልንሰራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ለማሳካት በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት በኃላፊነት እና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ አንስተዋል።

በዞኑ ገቢዎች መምሪያ ታክስ ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ቅሬታ አጣሪ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ገነነ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የግብር ከፋዮች መረጃ አለማደራጀት፣ ውዝፍ ዕዳዎችን አሟጦ አለመሰብሰብ፣ የደረሰኝ ክትትልና ቁጥጥር ማነስ የተስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው።

በታቀደው ልክ ገቢን ለመሰብሰብ ከዚህ በፊት በገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም የአሰባሰብ ሥርዓታችንን በማዘመን የገቢ አማራጮች ላይ በትኩረት እና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ያነጋገርናቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች በ2017 የተስተዋሉ ችግሮችን በማረም በየመዋቅራቸው ፍትሀዊ የሆነ የግብር አሰባሰብ ስርዓትን በመከተል የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በመድረኩ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ መዋቅሮች የዋንጫና የሰርተፊኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የ2018 የግብ ስምምነት ፊርማ በመምሪያውና በታችኛው መዋቅር ባሉ አመራሮች ተፈጽሟል።

ከመድረኩ በተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች ዙሪያ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ መድረኩ ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን