በኮንሶ ዞን የከና ወረዳ -ደበና -ከመሌ የ 7 ነጥብ 54 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በይፋ ተጀመረ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ40 ሚሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የኮንሶ ዞን ከና ወረዳ -ደበና -ከመሌ የ 7 ነጥብ 54 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በይፋ ተጀምሯል።
የመንገድ ግንባታው መጀመር ያመረቱትን ምርት ለገበያ ከማቅረብ ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ያለው ፋይዳ ላቅ ያለ መሆኑን ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።
በኮንሶ ዞን የከና ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ከፋይ ገብሬና ገዛኸኝ ገሌቦ እንዳሉት የዘመናት ጥያቄ የነበረውን የመንገድ መሠረተ ልማት ምላሽ በመስጠት መንግስት ያደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመንገድ መሠረተ ልማቱ ሲጠናቀቅ ያመረትነውን ምርት ገበያ በማድረስ ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ባሻገር የህዝብ ለህዝ ትስስርን እንደሚያጠናክር ነዋሪዎቹ ገልፀዋል ።
በዚህ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የከና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ካርሾ ገዴኖ፥ የገጠር የመንገድ ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ለአከባቢው ነዋሪ ብሎም ለአርሶአደሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል ።
መንገዱ በርካታ ቀበሌያትን በማስተሳሰር በአከባቢው ለውጥ እንዲመዘገብ የሚያደርግ በመሆኑ ህብረተሰቡ ለመንገዱ ግንባታ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ያስተላለፉት ደግሞ የኮንሶ ዞን መንገድና ትራንስፖርት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ካሊታ ናቸው ።
የኮንሶ ዞን ም/አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራሾ ጎስኬ የመንገድ ጥያቄ ረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንደነበር አስታውሰው፥ መንግስት ባደረገው ጥረት የህዝቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ በመመለሱ ደስተኛ ሆነናል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ ብርሃኑ ጌቦ (ዶ/ር) ቢሮው ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር በ40 ሚሊየን ብር ወጪ የመንገድ ግንባታውን መጀመሩን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የተገነቡትን የማስተካከል እና 7 ነጥብ 54 ኪሎ ሜትር ጠረጋ እንደሚደረግ ጠቁመው፥ ይህም ለወረዳው ያለው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የኮሪደር ልማት ስራዎች ለከተማ ዕድገት ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ
በጎፋ ዞን በ2018 በጀት ዓመት ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ
የምዕራብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ በጀሙ ከተማ እያካሄደ ይገኛል