መስከረም 20/2018 ዓ.ም የሚከበረውን የሸካቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል/ማሽቃሬ ባሮ/ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት መጀመሩን የሸካ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
በ2017 የተከበረውን የማሽቃሬ ባሮና የጎንጓ ህዝቦች ፎረም አከባበርን የተመለከተ ሪፖርትና ቀጣይ በበዓሉ አካባበር ሁኔታ ላይ በአንድራቻ ወረዳ ጌጫ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ፤ አምና ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረውን የሸካቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል የተሳካ ለማድረግ የተጉትን ሁሉ አመስግነዋል።
በገንዘብ፣ በእውቀትና በቁሳቁስ አበርክቶ በማድረግ አይረሴ የታሪክ አካል የሆናችሁ የዞናችን ህዝቦችና አጋሮች የትውልድ ቅርስ ጥላችኋልና ክብር ይገባችኋል ብለዋል።
አምና የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር በ2018 ዓ.ም የሚከበረውን በዓል ስኬታማና ደማቅ ለማድረግ ህዝባዊ መሰረት ጥለን እንሰራለንም ብለዋል።
በውይይቱ የተገኙት የሸካ ንጉስ ታቶ ተቺ ቄጆቺ የሸካቾ ብሔረሰብ ባህላዊ አስተዳደርን ዳግም ከማቋቋም ጀምሮ የብሔረሰቡ ዘመን መለወጫ በዓል/ማሽቃሬ ባሮ/በተሳካና በደመቀ መልኩ እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱና እያበረከቱ ላሉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የ2018 ዓ.ም የሸካቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል/ማሽቃሬ ባሮ/በደመቀ መልኩ እንዲከበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ንጉሱ ጥሪ አቅርበው፤ ኮሚቴው ላከናወነው በጎ ስራ እውቅና ሰጥተዋል።
የፍቅርና የአብሮነት መገለጫ የሆነውን/ማሽቃሬ ባሮ/ን በተሳካ መልኩ ለማክበር ከአምናው ውስን ክፍተቶች በመነሳት ከወዲሁ አቅዶ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ አምና ተግባሩን በከፍተኛ ሀላፊነትና ዲስፒሊን የመሩት ኮሚቴዎች ተጨማሪ እገዛ ተደርጎላቸው ቀጣዩን በዓል እንዲያስተባብሩ ተሰይመዋል።
የሸካ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀመረ ተሰማ፤ በታሪክ አጋጣሚ የህይወት ገጻችን አካል የሆነውን በዓል ለማክበር ያሉንን ጸጋዎች በአግባቡ እንጠቀማለን ብለዋል።
የውይይቱ አጀንዳ አካል የነበረውን በአዲስ አበባ የሚከበረውን ንዑስ ዝግጅት በተመለከተ ውይይት ተደርጎ አዲስ አበባ የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችና ወዳጆች ባሉበት ሆነው በደመቀ መልኩ እንዲከበር ንጉሱን ጨምሮ በዋና አስተዳዳሪ ይሁንታ አግኝቷል።
በዚህም መሠረት የበአል አዘጋጅ ኮሚቴና የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አዲስ አበባ ከሚገኙ ወገኖች ጋር ሆነው ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ከስምምነት ተደርሷል።
ማሽቃሬ ባሮ የፊታችን መስከረም 20/2018 ዓ.ም በሸካ ንጉስ መናገሻ አንድራቻ (ጌጫ) ከተማ ላይ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።
ዘጋቢ፡ አስማማው ኃይሉ – ከማሻ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ
በ2018 ከ502 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ