ማረሚያ ቤቶች ከማረምና ማነፅ ሥራዎች በተጨማሪ የልማት ሥራዎችን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ገለፀ

ማረሚያ ቤቶች ከማረምና ማነፅ ሥራዎች በተጨማሪ የልማት ሥራዎችን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ገለፀ

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል የኑስ ሙሉ የተመራው ልዑክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኣሪ ዞን የሚገኘውን የጂንካ ማረሚያ ተቋም የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል የኑስ ሙሉ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለፁት፤ የጂንካ ማረሚያ ተቋም ከማረምና ማነፅ ሥራው ጎን ለጎን አጫጭር ስልጠናዎችን ለታራሚዎች በመስጠት ያከናወናቸው የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ፤ በክልሉ የሚገኙ የማረሚያ ተቋማት የሕግ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አስረድተዋል።

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው የማረሚያ ቤቱን ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ለማጠናከር በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የጂንካ ማረሚያ ተቋም ዋና አዛዥ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ኔሬሬ እንደገለፁት፤ በተቋሙ የሚገኙ ታራሚዎች አያያዝ ዙሪያ ከታራሚዎች፣ ከጥበቃ አባላትና ከተቋሙ አመራሮች ጋር በመወያየት የተሻለ ግንኙነት ተፈጥሯል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን