የቱርሚ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመደበኛና በማታ መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን 334 ተማሪዎችን በደረጃ አራት አስመረቀ

የቱርሚ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመደበኛና በማታ መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን 334 ተማሪዎችን በደረጃ አራት አስመረቀ

ኮሌጁ በእንስሳት ጤናና እርባታ በሰብል ልማት፣ በቱሪዝም እና በኮምፒውተር የስልጠና ዘርፎች በደረጃ-4 ያሰለጠናቸውን ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመረቀው።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ በመርሐ ግብሩ ተገኝተው ለተመራቂ ሰልጣኞችና ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮሌጁ በአርብት አደር አካባቢ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን በትምህርት ልማት ዘርፍ ቀጣይ ለውጥ እንዲመዘገብ በልዩ ሀላፊነት እንዲሠራ አቶ ማዕከል አሳስበው ፤ ለተቋሙ የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረጉ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ሀላፊና የዕለቱ ክብር እንግዳ አቶ ዳዊት ፋንታዬ፤ በሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማትን ለማረጋገጥ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት እየሠሩ ይገኛሉ ብለው ከእነዚህም መካከል አንዱ የቱርሚ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አንዱ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ ከገበያ ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ ስልጠና አግኝተው ወጥተው እንዲሰሩ እየተደረገ ሲሆን ተመራቂዎች በአካባቢው ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በሰለጠኑት ልክ ህዝቡን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

ወደፊት ተመራቂ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት ኢንተርፕርነርሽፒ ስልጠና አግኝተው እንዲበቁ ይደረጋል ሲሉም የቢሮ ሀላፊው ተናግረዋል።

በደቡብ ኦሞ ያሉ የቱርሚና የሌሞ ጌንት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተሻለ ቁመና ለዜጎች ስልጠና እንዲሰጡ ልዩ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና መምሪያ ሀላፊ አቶ ተፈራ ናስኬ፤ ኮሌጁ በሀገሪቱ በመካከለኛ የሰለጠነ የሰው ሀይልን ለማፍራት በሚደረገው ትኩረት አንዱ አካል ሆኖ የተጣለበትን ሀላፊነት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

የተመረቁ ሰልጠኞችም ስራ ጠባቂ ሳይሆን ፈጣሪ በመሆን ራሳቸውንና አካባቢውን የሚያገለግሉ መሆን አለባቸው ሲሉም የመምሪያ ሀላፊው አሳስበዋል።

የቱርሚ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የኮሌጁ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሐማ አይኬ፤ ተመራቂ ተማሪዎች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ህዝቡን እንዲያገለግሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል 34 የሚሆኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቆላማና መስኖ ልማት ቢሮ ሙሉ ወጪያቸው ድጋፍ ተደርጎላቸው የተማሩ ስለመሆናቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አይደ ሎሞዶ ገልፀዋል።

ቢሮው ከአጫጭር ስልጠናዎች በተጨማሪ እስከ ዶክትሬት ድረስ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ያለባቸው አካላትን በመለየት እያስተማረ እንደሚገኝም አቶ አይደ ተናግረዋል።

የቱርሚ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዲን አቶ ሲሳይ ደጉ ለምረቃ የበቁ ሰልጣኞችን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮሌጁ ከመደበኛ ስልጠና በተጨማሪ አጫጭር ስልጠናዎች ለአካባቢው ማህብረሰብ ክህሎትና ዕውቀት ሽግግር ማድረጉንና ይህንንም እያካሄደ እንደሚገኝ ዲኑ ገልፀዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በኮሌጁ በአካል በመገኘት ካደረጉት ምልከታ በኋላ ለተቋሙ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርገዋል ሲሉም ዲኑ ተናግረዋል።

የአካባቢውን ችግር በጥናት አስደግፎ በመለየት ይህንን ወደ ሙያ ስልጠና እንዲካተት እየሠራ የሚገኝ ኮሌጅ ነው ያሉት ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደ ፖሊ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ደረጃ ለመሸጋገር ተግቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ኮሌጁ በመደበኛና በማታ መርሐ ግብር ያሰላጠናቸውን ማስመረቁንም ገልፀዋል።

ተመራቂ ተማሪዎችም በኮሌጁ በቂ ዕውቀትና ክህሎት መጨበጣቸውን ገልፀው ወደ ማህብረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት በታማኝነትና በትጋት እንደሚሠሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂ ተማሪዎች ከዕለቱ ክቡር ዕንግዶች እጅ የተዘጋጀላቸውን ዕውቅናና የምስክር ወረቀት ተረክበዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን