የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 03/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኋላቀር የግብርና አሰራር ዘዴን ለማሻሻል የሚያግዙ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንዳለ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት በኣሪ ዞን ደቡብ ኣሪ ወረዳ ከ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የግብርና ግበዓቶችን ድጋፍ አድርጓል።
በግብርናው ዘርፍ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው አደይ የተሰኘዉ መንግስታዊ ፕሮግራም በኣሪ ዞን ደቡብ ኣሪ ወረዳ በግብርና ዘርፍ ተደራጅተው ለሚሰሩ ወጣቶች ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የግብርና ግበዓቶችን በማቅረብ፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በመሰራትና በሌሎችም ድጋፍ በማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የኣሪ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ አባተ አስታውቀዋል።
በ2018 ምርት ዘመን በግብርና ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ሥራ ለሚገቡ 28 ኢንተርፕራይዞች ከ1.6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው 8 የዉሃ ፓምፖች፣ የተለያዩ የጓሮ አትክልት ዘር፣ የእርሻ መሣሪያ፣ ቆርቆሮ፣ ጀኔሬተር እና ሌሎች የተለያዩ የግብርና መሣሪያዎችን በፕሮግራሙ ድጋፍ መደረጉን አቶ ሙሉጌታ አመላክተዋል።
በድርጅቱ የሚደገፉ ወጣቶች አመለካከት እና የሥራ ባህል እየተሻሻለ መምጣቱንና የኢኮኖሚ አቅማቸውንም በማሳደግ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸዉን እየደገፉ መሆናቸውን አመላክተው፤ በቀጣይ ዞኑ ከመሠል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ድጋፉን እያሳደገ እንደሚሄድ አመላክተዋል።
የደቡብ ኣሪ ወረዳ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ካሡ ቡርዚዳቦ፤ ፕሮጀክቱ ከወረዳዉ ጋር በመሆን ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተደረገ ላለው ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በፕሮጀክቱ እየተደረገላቸዉ ባለው ድጋፍ ውጤታማ መሆናቸዉን በዶሮ ዕርባታ የተደራጁ ማህበር አባላት ተናግረዋል።
የደቡብ ኣሪ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ እና የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሸናፍይ ደይዳቅ ድርጅቱ እያደረገ ላለው ድጋፍ በወረዳዉ ስም አመስግነው፤ በቀጣይ ከፕሮጀክቱ ጋር በመተባበር ወጣቶች ተጨባጭ ለዉጥ አምጥተዉ የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ መላኩ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ
በ2018 ከ502 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ