የጉራጊኛ ቋንቋን በማልማትና በማስተዋወቅ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጉራጊኛ ቋንቋን በማልማትና በማስተዋወቅ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ከጉራጌና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖች ለተወጣጡ የጉራጊኛ ቋንቋ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ሀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር መለሰ እጥፉ እንደገለፁት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃገር በቀል እውቀቶችና በሌሎች ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ቋንቋን ማሳደግ ሁሉን አቀፍ እሴቶች ማሳደግ እንደመሆኑ ሰልጣኞች በሚቆዩበት የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚገባቸውን እውቀት እንዲጨብጡ ይደረጋል ብለዋል።
ስልጠና መምህራን የቋንቋዉ ማስተማር ስነ ዘዴዎች እንዲሁም የማስተማሪያ መፅፍት ላይ ከማስተዋወቅ ባለፈ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጥርላቸው ታስቦ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የቋንቋ ባህልና የሃገር በቀል እውቀቶች ልማት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን ናቸው።
ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ባሻገር ከሚጠበቅባቸው ተልእኮዎች መካከል በአካባቢው ያሉት ሃገር በቀል እውቀቶችን እንዲተዋወቁ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው አንስተው ሰልጣኞችም በትኩረት መከታተል አለባቸው ብለዋል።
የጉራጊኛ ቋንቋ መበልፀግ ለታዳጊዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የሚያግዛቸውና መምህራንም የተዘጋጁትን መፅሃፍት በተገቢው ተረድተው ማስተማር እንዲችሉ ስልጠናው አጋዥ እንደሚሆን የተናገሩት ከምስራቅ ጉራጌ ዞን በአሰልጣኝነት የመጡት ወ/ሮ ስንታለም ሲጃ ናቸው።
ከሰልጣኞች መካከል መ/ርት ሙሉነሽ ኬርጋ፣ የምስራች በየነ እና መ/ር አለነ ዘመዱ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በቋንቋው ሲያስተምሩ ሲያጋጥሟቸው የነበሩትን ክፍተቶች ሊሞላ የሚችል ስልጠና እንደሚሆን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው ከጉራጌና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖች ለተወጣጡ የጉራጊኛ ቋንቋ መምህራን እየተሰጠ የሚገኘው የአቅም ግንባታ ስልጠና ለ30 ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ መሃሪ አብድልከሪም – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በኪነ ጥበብ ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ
በ2018 ከ502 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ