“በእጅ ጋሪ ያመላልሱኝ ነበር” – ተወዳ መንጌ

“በእጅ ጋሪ ያመላልሱኝ ነበር” – ተወዳ መንጌ

በደረሰ አስፋው

የአካል ጉዳት ከአላማዋ ወደ ኋላ አልጎተታትም፡፡ እንዲያውም ለብዙዎች የጽናት ምሳሌ ናት፡፡ አትችልም የተባለውን ችላ አሳይታለች፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርስቲ ባለፈችባቸው የትምህርት ጊዜያቶች ፈታኝ የተባለውን ጉዞ አልፋ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተመርቃለች፡፡

“ህይወት ጥንካሬን፣ ጽናትን አስተምሮኛል” ያለችው የዛሬው የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን ከግል ጥረቷ ባሻገር ቤተሰቦቿ ለሷ የነበራቸው ፍቅርና እንክብካቤም ለዛሬው ህይወቷ መሰረት የጣለ ነው፡፡

አትችልም የሚል አስተሳሰብ አልነበራቸውም፡፡ በቤት ውስጥ እንጀራ መጋገር፣ ቤት ማጽዳት፣ ልብስ ማጠብ እና ሌሎች ስራዎችን ትሰራ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ጥንካሬን እንዳጎናጸፋትና ለዛሬው ህይወቷ እንደጠቀማት ነው የምትናገረው፡፡

ወ/ሮ ተወዳ መንጌ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በወላይታ ዞን በሚገኝ አንድ የገጠር ቀበሌ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በዚሁ የትውልድ ቀዬዋ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምራለች፡፡ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የተማረችው ወደ ወላይታ ሶዶ በመምጣት ቤት ተከራይታ ነው፡፡ የ12ኛ ክፍል ውጤት ከ300 በላይ በማምጣት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ለአራት አመታት የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቃ በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች፡፡

የቤተሰቡ 5ኛ ልጅ ስትሆን ወላጅ እናቷ የቤት እመቤት፣ አባቷ ደግሞ ታታሪ አርሶ አደር ናቸው፡፡ በቤተሰቡ መካከል ወላጅ እናቷ በቤት ውስጥ የተለያዩ ሙያዎችን አስተምረው ህይወቷን እንድትመራ ፍላጎት ነበራቸው፡፡

ወላጅ አባቷ ደግሞ ፊደል ቆጥረው የትምህርትን ጣዕም የቀመሱ ባይሆንም ስለ ትምህርት ያላቸው ግንዛቤ ግን የተለየ እንደነበር ታወሳለች፡፡ አለመማራቸውም ይቆጫቸው ስለነበር ሁሉንም ልጆቻቸውን አስተምረዋል፡፡ በተለይ ከጊዜ በኋላ አካል ጉዳተኛ የሆነችባቸው ልጃቸው ተወዳ እንድትማር የነበራቸው ጉጉት የተለየ ነበር፡፡

ተወዳ እስከ 6 አመቷ ሙሉ አካሏ ጤነኛ ነበር፡፡ ለወላጆቿ እየተላላከች በስራ ታግዝ ነበር፡፡ ከእኩዮቿም ጋር ትጫወት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከእለታት በአንዱ ቀን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ ህመም ተሰማትና ከወላጅ እናቷ ጋር በእግሯ ለህክምና ወደ ጤና ተቋም ሄደች፡፡ ስትመለስ ግን በወላጅ እናቷ እንደ ህጻን ታዝላ ተመለሰች፡፡

መርፌ ስትወጋ በተፈጠረ የህክምና ስህተት ሁለቱም እግሮቿ መንቀሳቀስ ተሳናቸው፡፡ በዚህ ህመም ለአራት አመታት የአልጋ ቁራኛ ሆነች፡፡ ትምህርት ለመግባት ዝግጅት ለምታደርገው ተወዳ እና ቤተሰቦቿም ድንጋጤና ሀዘን መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ከአራት አመታት ህመም በኋላ ግን ሁለቱ እግሮቿ የመንቀሳቀስ ሀይል ቢሳናቸውም በእንፉቅቅ በመሄድ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ ይህ ደግሞ ለተወዳ እና ቤተሰቡ አዲስ ተስፋን ይዞ መጣ፡፡ አካል ጉዳቱ ጫና ቢኖረውም ትምህርት ቤት ለማስገባት ወደ ኋላ አላሉም፡፡ በተለይ የወላጅ አባቷን ድጋፍ በቃላት ከምትገልጸው በላይ እንደሆነ ነው የተናገረችው፡፡

“አባቴ ከእርሻ ሲመለስ የእጅ ስራ ስሰራ ሲያይ ይጣላ ነበር፡፡ የምሰራውን ሁሉ ከእጄ ነጥቆ ይጥላል፡፡ ሙያውን ጠልቶ ሳይሆን ትምህርት እንዳትማር ያደርጋል በሚል እንጂ። በዚህም ከእናቴ ጋር ይጋጩ ነበር” ስትል ነው የተናገረችው፡፡

በዚህ መሀል ግን ቤተሰቦቿ ለስራ አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ወልቂጤ ሄዱ። በአካባቢው የነበረው ወንዝ ደግሞ ተወዳ ትምህርት ቤት እንዳትገባ እንቅፋት ሆነባት። ወላጅ አባቷ የነበራቸውን ሀብትና ንብረት ጥለው ወደ ቀድሞ ቀያቸው ሊመለሱ እንደቻሉ ነው የተናገረችው፡፡

ወደቀዬያችን እንደመጣንም የመጀመሪያ ስራው እኔን ትምህርት ቤት ማስገባት ሆነ፡፡ አንደኛ መንፈቅ አልቆ የ2ኛ መንፈቅ ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ ተሸክሞ ወስዶ መዝግቡልኝ አለ፡፡ በሚቀጥለው አመት መስከረም ላይ አምጡ አሁን አመቱ ተገባዷል ቢሉትም እሱ ግን መስማማት አልቻለም፡፡ ‘ልጄ አሁንም ተምራ ማለፍ ትችላለች መዝግቡልኝ’ በሚል ትምህርት ቤት ጥል ተፈጥሮ ነበር” በማለት ትናገራለች፡፡

የትምህርት ዘመኑ ደርሶ ከተመዘገበች በኋላ ተወዳን ትምህርት ቤት ለማመላለስ ያሰቡትም በእጅ ጋሪ ነው፡፡ ተሰባብሮ የተጣለን የእጅ ጋሪ ጠግነው አዘጋጁ፡፡ በጋሪ ጭነው በመውሰድ ትምህርት እንድትጀምር አደረጉ፡፡

ከቤት ወጥታ ስትማር ለማየት የነበራቸው ምኞት ተሳካ፡፡ ከ40 ደቂቃ በላይ በሚፈጀው ርቀት በጋሪ እየገፉ ትምህርት ማስገባታቸው በብዙዎች ዘንድ አድናቆት ተቸራቸው፡፡

“ከጊዜ በኋላ ግን አብረውኝ የሚማሩ ተማሪዎች ከአባቴ ተቀብለው በጋሪ እየገፉ ሁልጊዜ ትምህርት ቤት ለመውሰድና ለመመለስ ይሽቀዳደሙ ነበር፡፡ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ስማር በዝናብ ቢሆን በጭቃ ጓደኞቼ ተሰላችተው አያውቁም፡፡ እንደመታደል ሆኖ ዛሬም የሰው ፍቅር አለኝ” ስትል ታክላለች፡፡

ወደ 9ኛ ክፍል አልፋ ወላይታ ሶዶ ከተማ ስትማር ዊልቸርም ሆነ የአካል ድጋፍ አልነበራትም፡፡ በመንፏቀቅ ከቤት ወደ ትምህርት ቤትና ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ትመላለስ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከድካሙ ባሻገር በእጇ ላይ የሚፈጥረው ቁስለት ፈታኝ ነበር። አስፓልቱ ያቃጥላት ነበር፡፡ ጠጠሩና እሾኩ ይወጋት ነበር፡፡ ችግሯን የተረዱት ቤተሰቦቿም የፈረስ ጋሪ ተከራዩላት፡፡

በዚህ ላይ እያለች ግን አንድ መልካም ዜና ሰማች፡፡ ችግሯን የሚያቀልላት ዊልቸር በአርባ ምንጭ የአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ድጋፍ እንደሚደረግ ሰማች፡፡ ይህን ዕድል ለመጠቀምም ሁለት ወንድሞቿ ትራንስፖርት እስከሚገኝበት ቦታ በጀርባቸው እያዘሏት ይወስዷት እንደነበር ታስታውሳለች። የልቧ ደርሶም ዊልቸሩን አግኝታ ችግሯን እንዳቀለለላት ነው የተናገረችው፡፡

የ12ኛ ክፍል ውጤቷም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የምትገባበት ዕድል ፈጠረላት፡፡ ተወዳ ግን ወደ ሀዋሳ ለመምጣት ፍላጎት አልነበራትም፡፡ ይልቁንም ባለችበት አካባቢ በሌሎች የሙያ ዘርፎች ለመማር ነበር እቅዷ፡፡ ቤተሰቦቿ ግን ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ እንድትገባ ግፊት አደረጉ፡፡

ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስትገባ ቀደም ሲል የነበራትን ዊልቸር ይዛ አልመጣችም። ከመኝታ ቤት ወደ ክፍል የምትመላለሰው በመንፏቀቅ ነበር፡፡ በዚህም አስፓልቱ ሲግል አካሏ ላይ ጉዳት አስከተለባት፡፡

ትምህርቱን አቋርጣ ወደ ቤተሰብም ለመመለስ አስባ እንደነበር ታስታውሳለች። ጓደኛዋ ግን ወደ ቸሻየር ኢትዮጵያ ሀዋሳ ቅርንጫፍ በማቅናት የዊልቸር ድጋፍ እንድታገኝ አደረገች፡፡ ችግሯን የምትጋራ ጥሩ የልብ ጓደኛ ሆነቻት፡፡ ይህ ድጋፍ ጉልበት ሆናት፡፡

ትምህርቷንም በጽናት እንድትማር አደረገች፡፡ እስከ 4 ዓመት ድረስ ካለምንም መሰላቸትና ድካም አጋርነቷን ላሳየቻት ጓደኛዋም አድናቆትና ክብር እንዳላት ነው የገለጸችው፡፡

ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በአካውንቲንግ በመጀመሪያ ዲግሪ ብትመረቅም ስራ አላገኘችም፡፡ በሀዋሳ ከተማ ያልረገጠችው የመንግስትና የግል ተቋማት ደጅ እንደሌለ ነው የተናገረችው፡፡ የሚሰጣት መልስ “ለእናንተ የሚሆን ስራ የለም” የሚል ነበር፡፡

በዚህ ላይ እያለች የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ ጀመረ፡፡ ወደዚሁ አቅንታ ለመቀጠር ቻለች፡፡ የውስጥ አልባሳትን በሚያመርት ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥራ መስራት ጀመረች፡፡

ክፍያው ያን ያህል አጥጋቢ ነው ባትልም የስራ ዕድል በማግኘቷ ግን ለቀጠራት መስሪያ ቤት ምስጋና እንዳላት ትናገራለች፡፡ ለሷና ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ላደረገው ድጋፍም ተሸላሚ እንደነበር በማስታወስ፡፡

ለ6 ዓመታት በዚሁ ፋብሪካ ሰርታለች፡፡ በምታገኘው አነስተኛ ደመወዝ የቤት ኪራይ፣ የማህበራዊ ጉዳይና እለታዊ ወጪዎቿን ሁሉ ትሸፍን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ባለትዳር ለነበረችው ተወዳ እርግዝና በመከሰቱ ለወሊድ ወጣች፡፡ ከወሊድ በኋላ ፋብሪካው መቀጠል ሳይችል ቀረና ተዘግቶ በመውጣቱ ስራ አልባ ሆነች፡፡

“ትዳር ከእግዚአብሄር ነው፤ ይሁን እንጂ አካል ጉዳተኛ ስትሆን ለየት ያሉ ፈተናዎች አሉ፡፡ ራሳችንም የምንፈጥረው ችግር አለ። በትክክል እኔን ወዶኝ ነው ከኔ ጋር የሆነው የሚል ጥርጣሬ ይንጸባረቃል፡፡ አካል ጉዳተኛ በመሆንህ በአዕምሮህ የሚመጣ ትክክል ያልሆነ አስተሳሰብ አለ፡፡

“በዚህ አይነት የግል ምልከታ የራስን ደስታ ማጣትም አለ፡፡ በተመሳሳይ በቤተሰብ የሚንጸባረቅ ጫና አለ፡፡ እንዴት መጣ፣ ምን አይቶ ነው? የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በመሰረትኩት ትዳር ደስተኛ ነኝ። የአንድ አመት ከ2 ወር ልጅ አፍርተናል፡፡ በአራስነት ጊዜዬም ከባል ማግኘት የሚገባኝን ፍቅርና እንክብካቤ አግኝቻለሁ” ስትል በትዳር ዓለም የገጠማትንና አሁን ያለችበትን ደረጃ ትናገራለች፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ በሴት አካል ጉዳተኞች ማህበር ላይ በሚሰራ “ጆይ” እና “ሻይኒ ዴይ”    በሚባል መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ካሸርና የሴት አካል ጉዳተኞች የመብት ተሟጋች ሆና ትሰራ ነበር፡፡

ድርጅቱ በአጋርነት አብሯቸው ሲሰራ ቢቆይም በቅርቡ ግን የስራ ጊዜውን አጠናቋል። ይሁን እንጂ 300 ሴት አካል ጉዳተኞችን በመያዝ ለረጅም ጊዜ ሲሰራ የቆየው ማህበራቸው ዛሬም በስራ ላይ ነው፡፡

ማህበሩ በሴት የሚመራ ነው፡፡ የሴት አካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅም እንዲከበር የሚሰራም ማህበር ነው፡፡ በቤት ውስጥ የተደበቁት ወደ ውጭ እንዲወጡና የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ነው፡፡

በዚህ አመትም በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ዘርፍ በርካቶች ሙሉ ግብአትና ወጪያቸው ተሸፍኖ እንዲማሩ ተደርጓል። አውቀውም ይሁን በመታለል ላልተፈለገ እርግዝና ለተዳረጉ ሴት አካል ጉዳተኞች ድጋፍ ያደርጋል፤ የስነ ተዋልዶ ስልጠና ይሰጣል። አካል ጉዳተኞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቻቸው እንዲከበሩ ይሰራል፡፡

በማህበር መሰባሰባቸውም ከተለያዩ ተቋማት የትምህርትም ይሁን ሌሎች ድጋፎችን እንዲያገኝ ረድቷቸዋል፡፡ ተወዳ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለችም እሷ በምታገለግልበት ማህበር ውስጥ ለሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የድጋፍ ደብዳቤ በመጻፍ በርካታ አካል ጉዳተኞች በሳምንት መጨረሻና በማታው የትምህርት መርሃ ግብር የትምህርት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በ2017 ዓ.ም 10 አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይ የመብት ጥሰት የተከሰተባት ሴት አካል ጉዳተኛ ካለችም ከሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጋር በመሆን መብት የማስከበር ስራ ይሰራል፡፡

“አካል ጉዳተኞች በውስጣቸው የታመቀ አቅምና ችሎታ አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካል ጉዳተኞች የሚስተዋል ችግር አለ፡፡ ከመስራት ይልቅ መለመንን አማራጭ ያደረጉ አሉ፡፡ ችግሩ ያለው በሚሰጠው አካል ላይ ነው፡፡

“ችግርን ለዘለቄታው መፍታት ነው እንጂ ለጊዜው የሚሰጠው ገንዘብ ልመናን የሚያበረታታ ነው፡፡ ሳይሰሩ መስጠት ተገቢ ባለመሆኑ ሰርተው ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ግን ተገቢ ነው” ብላለች፡፡

ተወዳ ሀዋሳ ከመጣች በኋላ ከምትሰራቸው ስራዎች ጎን ለጎን ምግብ ቤት ከፍታ ሰርታለች፡፡ ሻይ ቡናም ሰርታለች፡፡ ኢንደስትሪ ፓርክ በነበረችበት ወቅት ከጧቱ 12 ሰአት እስከ ቀኑ 8 ሰአት ከሰራች በኋላ ያላትን ጊዜ ለመጠቀም ጥረት ታደርግ እንደነበርም ገልጻልናለች፡፡

ወደ ንግዱ ለመቀላቀል ተስፋ ነበራት፡፡ ይሁን እንጂ በወሊድ ወቅት ለኪሳራ በመዳረጓ ስራውን እንድታቆም ተገደደች፡፡ በመሆኑም አካል ጉዳተኞች ምቹ ነገር ካገኙ ሁሉን ይችላሉ የሚል ሀሳብ ስላላት ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ነው ያለችው፡፡