የ2018 ዓ.ም “ማሽቃሮ”ን ለዓለም ማስተዋወቅ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ነው
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የ2018 ዓ.ም “ማሽቃሮ”ን ለዓለም ማስተዋወቅ በሚያስችል መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የካፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ ወ/ሮ ታሪኳ ታከለ “ማሽቃሮ” የካፋ ህዝብ የሚታወቅበት ክብረ-በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደምት አባቶች የዓመቱን ተግባራት በመገምገም የአዲሱን ዓመት ዕቅድ ይፋ የሚያደርጉበት እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ ታሪኳ፥ የአሁኑ ትውልድ ይህንን እሴት እያስቀጠለ ነው ብለዋል።
የዘንድሮውን “ማሽቃሮ” ከአምናው በተሻለ መልኩ ህዝቡን በማሳተፍ ለማክበር የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ባህልን፣ ወግንና ቅርሶችን በተሻለ መልኩ ለዓለም ማስተዋወቅ በሚያስችል መልኩ ለማክበር መታቀዱን ጠቁመው፥ በዓሉ የሚከበርበት የጥንት ነገስታት መቀመጫ የሆነውን “ቦንጌ ሻምበቶ” ለማስዋብ ኮሚቴ በማዋቀር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዓሉ ከጎረቤት አካባቢዎች ባሻገር ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ተጋባዥ እንግዶችና ጎብኚዎች የምሳተፉበት በመሆኑ ፤ ለዚህ በሚመጥን መልኩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የገዋታ ወረዳ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተገኝ ማሞና የጊምቦ ወረዳ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሻለ ክፍሌ የዘንድሮውን “ማሽቃሮ” በዓል አከባበር ቅድመ-ዝግጅት ስራን በሚመለከት አስተያየታቸውን ለጣቢያችን ሰጥተዋል።
“ማሽቃሮ”ን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (UNESCO) ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ፤ ለዚህ በሚያግዝ መልኩ ለማክበር እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የበዓሉ አከባበር ድባብ ከዓመት ወደ ዓመት እየተሻሻለና እያደገ መምጣቱን አንስተው ፤ ካለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ ለማክበር ጥረት እያደረጉ እንደሆነ አክለዋል።
ዘጋቢ፡ ሀብታሙ ታደሰ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
በአካል ጉዳተኝነት ተስፋ ባለመቁረጥ የተገኘ ስኬት
ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ የውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
የህፃናትን ጤናማነት ለመጠበቅ ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ