በአሪ ዞን በሰሜን አሪ ወረዳ ከወቀት ጋማ ግቻ እስከ አፈነት ዎጫ 4 ቀበሌያት የሚያገናኝ የመንገድ ስራ እንደተጀመረ የዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ገልጸ

በአሪ ዞን በሰሜን አሪ ወረዳ ከወቀት ጋማ ግቻ እስከ አፈነት ዎጫ 4 ቀበሌያት የሚያገናኝ የመንገድ ስራ እንደተጀመረ የዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ገልጸ

በመንገድ ሥራ ማስጀመሪያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና ትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ብርሃኑ ገቦ እንደተናገሩ፤ መንገድ የልማት ሁሉ አውራ፣ የኢኮኖሚ ጀርባ አጥንት ስለሆነ የክልሉ መንግስት የመንገድ ችግር ያሉባቸውን አካባቢዎች በመለየት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

ስራውንም መንግስት ከዓለም ባንክ ገንዘብ ድጋፍ በተገኘ በምግብ ዋስትና ኘሮግራም(RCFSP) ጋር በመተባበር እንደሚያሰራ ገልጸዋል፡፡

የመንገድ ስራው በኢፍቦሩ ኮንስትራክሽን 9.7 ኪሎ ሜትር በ53 ሚለየን ብር በ6 ወር ሰርቶ ለማጠናቀቅ ውል ገብቶ ሥራውን እንደጀመረ ተናግረዋል።

መንገዱ የሚሰራበት አካባቢ በቡና፣ በኮረሪማ እና በዝንጅብል ምርት የሚታወቅ ስለሆነ መንገዱ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ለማህብረሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የሰሜን አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደግፋው ጌታቸው ገልጸዋል።

የሚሰራው መንገድ ከወቅት ጋማ ግቻ ቀበሌ እሰከ አፈነት ዎጫ 4 ቀበሌያትን የሚያገናኝ ስለሆነ የህዝቡን የእርስ በርስ ትስስርን የሚያጠናክርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ የመንገድ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ገልፀዋል።

መንገዱ ሲሰራ ማህበረሰቡ በመንገድ ዳር ያሉ እንደ ኮረሪማ፣ ቡና ወዘተ የመሳሰሉ ንብረቶች በማንሳት ለመንገድ ሥራ የሚመጡትን ማሽኖችን የመጠበቅና እንግዶችን የመቀበል ተግባራት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

ከመንገድ ችግር የተነሳ ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ ያልቻሉ አርሶ አደሮች የተጀመረው መንገድ ሲጠናቀቅ ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የሚረዳ ትልቅ እድል እንደሆነ የአሪ ዞን ትራስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገዛህኝ ጨነቀ ገልጸዋል፡፡

መንገዱ በክልሉ መንግስት በትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ገጠር ትስስር በምግብ ዋስትና ኘሮግራም(RCFSP) 4 ቀበሌያትን የሚያገናኘው 9.7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን መንገድ በክልል 53 ሚሊየን ብር ወጭ እንደተጀመረ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ሀብት መድቦ የሚሰራ በመሆኑ ህብረተሰቡ ማሽኖችን በመጠበቅና ለስራው ተባባሪ በመሆን እንዲሰራ የመምሪያ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት ከዚህ በፊት የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ የግብርና ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ ብሎም ወላድ እናቶች ለወሊድ አገልግሎት በቃሬዛ ሲሸከሙ መቆያታቸውን በመግለጽ የመንገድ ሥራው በመጀመሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ የተሰራው መንገድ እንዳይበላሽ በመጠበቅ እና በመንከባከብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ታገል ለማ – ከጂንካ ጣቢያችን