የኦሞ ወንዝና የቱርካና ሐይቅ በዳነሰች ወረዳ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለማስቀረት በጥናት የተደገፈ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሻ ተገለፀ

የኦሞ ወንዝና የቱርካና ሐይቅ በዳነሰች ወረዳ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለማስቀረት በጥናት የተደገፈ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሻ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኦሞ ዞን የኦሞ ወንዝና ቱርካና ሐይቅ በዳነሰች ወረዳ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለማስቀረት በጥናት የተደገፈ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሻ ተገለፀ።

ጉዳቱን ለመከላከል ከፌዴራል ጀምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጥምረት እየሠሩ ስለመሆናቸው የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊና የዞኑ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ምንላርገው አዲሱ ገልፀዋል።

በአሁን ወቅት ውሃው በአካባቢው የከፋ ቀውስ እንዳያስከትል በማሽነሪ የታገዘ ክትርና የዳይክ ሥራ የዞኑ አደጋ ስጋት ምክር ቤት ከክልልና ከፌዴራል በመንግስት ጋር በመቀናጀት እየሠራ እንደሚገኝም አቶ ምንላርገው አዲሱ አስረድተዋል።

ከ80 ሺህ በላይ ማህብረሰብ አካላት ከዳሰነች ወረዳ ከ34 ቀበሌያት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሲሆኑ ለእነዚህ አካላት ቀለብን ጨምሮ ሌሎች የጤናና መሰል ድጋፎችን ከፌደራል ጀምሮ በተዋረድ እስከ ወረዳ ድረስ በመናበብ እየቀረበ እንደሚገኝም ሀላፊው አረጋግጠዋል ።

በቀጣይ የተፈናቀሉ አርብቶ አደሮችንም ሆነ የከተማውን ነዋሪ አደጋው ሊያስከትል ከሚችል ጉዳት ለመታደግ የዞኑ አደጋ ስጋት ምክር ቤት ከፍ ካሉ መዋቅሮች ጋር በመነጋገር ቀጣይነት ያለው ሥራ እየተተገበረ እንዳለም አመላክተዋል።

በውሃ ሙላት የተፈናቀሉ አካላት ወንዙ በየጊዜው የሚያደርሰውን አደጋ መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ዘላቂ በሆነ መልኩ እንዲያስቀሩ ጠይቀው፥ በአሁን ወቅት ቀለብን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ እንደሚገኙ ተናግረው፥ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በዞኑ የሚሰሩ የሲቪክ ማህብረሰብ አካላት የጋራ መድረክ ቱርሚ ከተማ ካካሄዱ በኋላ ወንዙ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በስፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል።

አደጋው ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ቀጣይነት ያለው ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ በአካባቢው በሚሠሩበት ወቅት መገንዘባቸውን ጠቅሰው ከዚህ በፊት የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት እየሠራ ያለውን ተግባር ለመደገፍ የሲቭክ ማህብረሰብ አካላት በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ድጋፍ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የውሃ ሙላቱን ሁኔታ በስፍራው ተገኝተው የተመለከተቱት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሲቪክ ማህብረሰብ ድርጅቶች ዳይሬክተር ማሞ ሞልሶ በአካባቢው ያለውን ቀውስ ለመከላከል የክልሉ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የሲቪክ ማህብረሰብ አካላትም የሚያደርጉትን ሁሉ አቀፍ ድጋፍ በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አት ማሞ አሳስበዋል።

ምንም እንኳ ክልሉ አንፃራዊ ሠላም ያለበት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጥሮ አደጋ በጎፋ፣ ኣሪና ወላይታ ዞኖች የመሬት መንሸራተትና ናዳ ተከስቶ ጉዳት ማስከተሉን የጠቀሱት ሀላፊው፥ ለዚህም መላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ በማድረጋቸው መልሶ ማቋቋም ሥራው በጥሩ ሁኔታ መካሄዱን ገልፀው በአሁን ወቅትም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው ብለዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ያለውን ጉዳት ለማስቀረት ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣ አቶ ማሞ ጥሪ አቅርበዋል።

የሃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን የሲቪክ ማህብረሰብ አካላት በስፍራው ተገኝተው የውሃው ሁኔታን እንዲመለከቱ ላደረገው አስተዋጽኦም አቶ ማሞ አመስግነዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን