በዞኑ የሕብረተሠቡን ሠላም በማስጠበቅ ተጠቃሚነቱን ለማሣደግ እየተሠራ መሆኑን የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ ገለፁ
የየም ዞን ምክር ቤት 5ኛ ዙር 13ኛ ሥራ ዘመን 29ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሣጃ ከተማ አካሂዷል።
ከጉባኤው አስቀድሞ የምክር ቤቱ አባላት እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በሣጃ ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የኮሾ ፍራፍሬ ማሸጊያ ማዕከል፣ የክልሉ መንግስት ተቋማት ቢሮ ግንባታ፣ ያንጋሮ ሕፃናትና ወጣቶች ተሠጥኦ ማዕከል እና የሣጃ ከተማ ኮሪደር ሥራ የጉብኝቱ አካል ነበሩ።
የ2017 አስፈፃሚ ተቋማትን ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት ያቀረቡት የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሕብረተሰቡን ሠላም በማስጠበቅ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በ2016/17 ምርት ዘመን በበልግ እና በመኸር 27 ሺ 703 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለመሸፈን ታቅዶ 28 ሺ 121 ሄክታር መልማቱን ተናግረዋል።
ከዚህም 1 ሚሊዮን 068 ሺ 598 ኩንታል ምርት መገኘቱን አስረድተዋል።
በፍራፍሬ፣ በእንሠት፣ በማር እና አትክልት ምርት ከነበረበት የተሻለ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን በእንስሣት ዘርፍ ካለው አቅም ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ አፈፃፀም መመዝገቡን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
ለ5 ሺ 73 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን ሕገወጥ ንግድ ለመቀነስ ቁጥጥር እና ክትትል ተደርጎ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ከተለያዩ ገቢ አርዕስቶች 229 ሚሊዮን 617 ሺህ 250 ብር በመሠብሠብ የዕቅዱን 95 በመቶ ሲከናወን በግብርና በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች 31 አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ዞኑ መግባታቸውን ገልፀዋል አቶ ሽመልስ እጅጉ።
የትራንስፖርት አገልግሎት አሠጣጡን ለማዘመን የተሽከርካሪዎች ሠሌዳ የመለጠፍና የከተሞችን ፕላን የማዘመን ሥራ ተሠርቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በተጠናከረ መልኩ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሕብረተሠቡን ባህልና ዕሴት በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከክልሉ እንዲሁም ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጥናት መደረጉን ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራት ለማሣደግ የተለያዩ ሥልጠናዎችን የመስጠትና የመማሪያ ክፍሎች ጥገና እንዲሁም አዳዲስ ክፍሎች ተሠርተዋል ብለዋል።
ቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትል በቤተሠብ ዕቅድ አገልግሎት አጠቃቀም ዝቅተኛ አፈፃፀም የታየ ሲሆን በጤና መድን ዋስትና የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ሠላም ለማስጠበቅ መረጃ በማደራጀት ወንጀልን ቅድሚያ የመከላከል ሥራ ይሠራል ያሉት አሰተዳዳሪው፤ በ2018 በጀት ዓመት አምና የታዩ ደካማ ጎኖችን በመገምገም የእንስሣት ሃብት የፍራፍሬ ልማት አዳዲስ አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሥራ ዕድል የመፍጠርና ኢኮኖሚን የሚያሣድጉ ተግባራት ላይ ትኩረት ተሠጥቶ ይሠራል ብለዋል።
የየም ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወሮ ዝናሽ ገ/ሥላሴ፤ የዞኑን ሕዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሁሉም ዘርፍ ልማት ለማሳለጥ ሁሉም መነሣሣት አለበት ብለዋል።
ከግብርና ልማት ጎን ለጎን ኢንዱስትሪውን በትጋት በመሥራት የሥራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለዚህም የምክር ቤት አባላትና ባለድርሻ አካላት በትኩረት መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በተለይም የየም ብሔረሰብ ልዩ መለያ የሆነውን የሄቦ በዓል አከባበር እና ሣመ ኤታ መድሃኒት ለቀማ ኩነትን በትኩረት መሥራት እንደምያስፈልግ አሣስበዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀው በየአካባቢው የሚታዩ የመንገድ፣ የውሃና የመብራት ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙበት መንገድ መፈለግ አለበት ብለዋል።
የ2018 በጀት ዓመት የዞኑ በጀት 529 ሚሊዮን 519 ሺህ 286 ብር ሆኖ የፀደቀ ሲሆን አቶ መንግስቱ ሲሣይ የየም ዞን ምክር ቤት ኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ አቶ አብዱጀሊል ሀሠን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ ገዛኽኝ ረጋ የዞኑ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ መዝሙረ ከበደ የዞኑ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል።
ዘጋቢ፡ ማሙዬ ፊጣ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 የትምህርት ዘመን የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች እና የ3ኛው ዙር “ትምህርት ለትውልድ” ማስጀመሪያ መድረክ በወራቤ ከተማ እየተካሄደ ነው
የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት “ኦገት” ለዘመናዊ የፍትህ ስርዓት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
ከ1 መቶ ሺህ በላይ መራጮች የ2017 የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምርጫ እንደሚሳተፉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ